አልሻባብ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል ላይ ጥቃት አደረሰ

A Ugandan soldier patrols a back street in the southern town of Merka, 90km north of Somalia"s capital Mogadishu, on 17 July 2016.

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የህብረቱ ሰላም አስከባሪዎች ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ናቸው።

አልሻባብ ከሞቃዲሾ በስተደቡብ ምእራብ በምትገኘውና ቡላማረር በተሰኘችው ከተማ የሚገኘው የህብረቱ ሰላም ማስከበር ቡድን ላይ ጥቃት ያደረሰው በጥይትና በቦምብ ነው።

ከጦር ሃይሉ ጣቢያ ውጭ የነበሩ ሁለት የጦር ሃይሉን መኪኖችም አጋይቷል።

የአካባቢው ኗሪዎች ለሶስት ሰዓታት የዘለቀ ከባድ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ገልፀዋል።

በተኩስ ልውውጡ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ በርግጠኝነት የታወቀ ነገር ባይኖርም ከሁለቱም ወገን ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

የሶማሊያ የአገር ውስጥ ፀጥታ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አብዱላዚዝ አሊ ኢብራሂም ዚልዲባን ለቢቢሲ እንደገለፁት 20 የአልሻባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ታጣቂዎቹ ወደ ሰላም አስከባሪ ሃይሉ ጣቢያ መዝለቅ አልቻሉም። በርካታ ጥይቶችንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎቻቸውንም መውሰድ ተችሏል።

ባለፉት ቅርብ ጊዜያት የእስልምና ታጣቂዎቹ በይዞታቸው ስር የነበሩ የሶማሊያን ከተማማዎች ሁሉ እንዲለቁ መደረጋቸው ይታወቃል።