ቻይና ከአሜሪካ በሚመጡ ምርቶች ላይ የሶስት ቢሊዮን ዶላር ቀረጥ ጫነች

Bottles of California wines are displayed on a shelf at John and Pete's Fine Wine and Spirits on February 14, 2017 in Los Angeles, California.

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአሜሪካ ወደ ቻይና በሚገቡ ወይንና የአሳማ ስጋ የመሳሰሉት 128 የምርት አይነቶች ላይ ቻይና 25% ቀረጥ ጫነች።

ይህ ውሳኔም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚሁ ወር ከውጭ በሚገቡ ብረትና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ ቀረጥ መጨመራቸውን ተከትሎ ነው።

ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ምርቶች ላይ ተፅእኖ የሚያመጣው ይህ ውሳኔም ከዛሬ ጀምሮ ተግባር ላይ ይውላል።

ውሳኔውንም አስመልክቶም ቤጂንግ የቻይንን ጥቅም ለማስከበር እንዲሁም አዲሱ የአሜሪካ ቀረጥ ያስከተለውን ኪሳራ ለማስመለስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቻይና ቀደም ባሉት ጊዜያት የንግድ ጦርነት እንደማትፈልግ ብታሳውቅም ኢኮኖሚዋ ሲጎዳ ግን እጇን አጣጥፋ እንደማታይ ገልፃ ነበር።

ትራምፕ በበኩላቸው የንግድ ጦርነት ጠቃሚነት ላይ አስምረው ለአሜሪካም ማሸነፍ ቀላል ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ በአስር ቢሊዮን ዶላር ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጨመር እቅድ እየነደፉ እንደሆነ የቢቢሲው ክሪስ በክለር ከዋሽንግተን ዘግቧል።

በቻይና ባለው ኢፍትሀዊ የንግድ ስርዓት ብዙ የአሜሪካ ኩባንያዎች እንደተጎዱ ገልፆ ይህ ግን በአሁኑ ወቅት ወደ ንግድ ጦርነት ተቀይሯል ብሏል።

የትኞቹ ምርቶች ይጎዳሉ?

ካሉት ምርቶች በተጨማሪ የአሜሪካው አሉሚኒየምና የአሳማ ስጋ ተጨማሪ 25% ቀረጥ ይጫንባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኦቾሎኒ፣ የደረቁ ፍራፍሬዎች እንዲሁም የወይን ምርቶች ላይ 15% ጭማሪ ቀረጥ ተጭኖባቸዋል።