በአማርኛ የሚያንጎራጉረው ፈረንሳያዊ

ልጅ ሊዮ እየዘፈነ

'ልጅ ሊዮ' በሚለው በመድረክ ስሙ የሚታወቀው ሌዮናር በተለያዩ መድረኮች ላይ ከብዙ ታዋቂ ዘፋኞችም ጋር ተጫውቷል።

አማርኛ አቀላጥፎ የሚናገረው ልጅ ሊዮ የፈረንሳይ ዜግነት ያላቸው ቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ለሥራ ሲመደቡ እሱም አዲስ አበባን ረገጠ።

ምንም እንኳን የተማረው 'ሊሴ ገብረ ማሪያም' የፈረንሳይ ትምህርት ቤት ቢሆንም ለአማርኛ ቋንቋ ፍቅር ያደረበት በልጅነቱ ነው።

በቤታቸው ከነበሩት ሠራተኞችና ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር እየተነጋገረ ቀስ በቀስ አማርኛ ለመደ።

አባቱ በኢትዮጵያ የነበራቸውን የ7 ዓመት የሥራ ቆይታ ጨርሰው ወደ ሌላ ሃገር ቢሄዱም ሊዮ ግን ለአማርኛና ለኢትዮጵያ የነበረው ፍቅር አልጠፋም።

ከአባቱ ጋር ከሀገር ሀገር እየተዘዋወረ ያደገው ሊዮ ቋንቋ ለማወቅ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ፈጣንም ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ አማርኛን ለመማር ወሰነ።

አማርኛ ቋንቋን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክም የተማረው ሊዮ ሁለተኛ ዲግሪውን ቢይዝም ቋንቋውን በደንብ ለማወቅና አቀላጥፎ ለመናገር 10 ዓመታት እንደፈጀበት ይናገራል።

ሊዮ በየ10 ዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመላለስ ሲሆን ከሙዚቃው በተጨማሪም የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል።

"ኢትዮጵያ ለኔ ሃገሬ ነች፤ ልቤም ኢትዮጵያዊ ነው" ይላል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ መኖሩና በምግብ ቤቱ ከሚያስተዳድራቸው ሠራተኞች ጋር በአማርኛ ብቻ መግባባቱ ቋንቋውን እንዲያዳብር እንደረዳው ይናገራል።

ይህም አማርኛውን ለማሻሻል ከመጥቀሙም ባሻገር ለሙዚቃዬም አስተዋጽዖ አድርጓል ይላል።

በተለይም ልጅ እያለ ከእኩዮቹ ጋር አብሮ ማሰለፉ አማርኛውን እንዲያሻሽል እንደረዳው ያስታውሳል።

''ከግቢ መውጣት ባይፈቀድልንም እንኳን በምኖርበት የሾላ ሰፈር ልጆች ብዙ ተምሬያለሁ፤ ከዚያም በተጨማሪ ብዙ ጊዜዬን ከዘበኛው ጋር አሳልፍ ነበር። ሬድዮ ሲያዳምጥም ካጠገቡ አልርቅም ነበር። ይሄም ብዙ ረድቶኛል '' ይላል

አድጎ ዩኒቨርሲቲ ከገባም በኋላ ከልጆች ጋር ወደ ጭፈራ ቤት በሚሄድበትም ወቅት በባህላዊ ሙዚቃ ይወዛወዝ እንደነበር ይናገራል።

ትናንቱን መለስ ብሎ በማስታወስም ''እኔ ከኢትዮጵያ ብወጣ እንኳን ኢትዮጵያ ግን ከሰውነቴ አትወጣም'' ይላል።

ነዋሪነቱን በፈረንሳይ መዲና ያደረገው ልጅ ሊዮ የሙዚቃ አልበሙን በመሥራት ላይ ነው።

"በፈረንሳይም ቢሆን አማርኛን የሚያናግሩኝ ሐበሾች አላጣም፤ ከአማርኛ አልፎ ክትፎ የሚጋብዙኝ ጓደኞችን አፍርቼያለሁ" በማለት በሳቅ ታጅቦ ይናገራል።

አማርኛ እንዳይጠፋበትም በስካይፕም ሆነ በቫይበር ከኢትዮጵያዊ ጓደኞቹ ጋር እንደሚያወራ የሚገልጸው ልጅ ሊዮ አልፎ አልፎ ደግሞ በዩ ቲዩብ ላይ የተለያዩ የአማርኛ ዝግጅቶችን ፊልሞችንና ሌሎችንም በአማርኛ የተሠሩ ቪድዮዎችን ይከታተላል።

ለሙዚቃ ለየት ያለ ፍቅር እንዳለው የሚናገረው ሊዮ ሰሜቱን ማንፀባርቅም ሆነ ማስረዳት የሚችለው በሙዚቃ ብቻ እንደሆነ ይናገራል።

''በተፈጥሮዬ ዜማ በውስጤ ይሽከረከራል። ብዙ ጊዜ መጀመሪያ ዜማው ነው የሚመጣልኝ'' ይላል።

ዜማው አንዴ መስመር ከያዘለት በኋላ ግጥሞቹን ከኢትዮጵያዊ ጓደኛው ጋር አብሮ በመሆን እያስተካከሉ ሙዚቃውን ያቀናብራሉ።

የሙዚቃ ፍቅሩ የተፀነሰው በልጅነቱ እንደሆነ የሚናገረው ሊዮ ሙዚቃ ለእርሱ ትልቅ ስፍራ እንዳለው ይናገራል።

''ለሰውነት ምግብ እንደሚያስፈልግ ሁሉ ለአዕምሮም ምግብ ያስፈልጋል፤ ለእኔ ደግሞ ሙዚቃ እንደ ምግብ ነው'' ይላል።

ሬጌ ሙዚቃ ማዳመጥ የሚወደው ሊዮ እራሱን በአንድ ሙዚቃ አይወስንም በተቃራኒው የተለያዩ ሃገራት የመኖር ልምዱን የሚገልጽበት አንዱ መንገድ በሙዚቃ ነው።

''ይህች ዓለም የተለያዩ ሃገራት አላት። እኔ ደግሞ በብዙ ሃገራት ነው ያደኩትና ያንን ሁሉ ማንፀባርቅ የምችለው በሙዚቃዬ ነው'' በማለት ያብራራል።

አሁን ሙዚቃ ላይ ብቻ እያተኮረ እንዳልሆነ የሚያስረዳው ሊዮ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት እንደ ማንኛውም ሰው መኖር እንደሚፈልግ ተናግሯል።

የሚወደውን ሙዚቃም ለመሥራትም በዚሁ ምክንያት ጊዜ እንደፈጀበት ያስረዳል።

ሙዚቃን ተገዶ ሳይሆን እሱ ሲያሰኘው የሚሠራው ሊዮ ለወደፊቱ በየሃገራቱ እየዞረ ሙዚቃውን የማቅረብ ዕቅድ አለው።

አሁንም ቢሆን በሚኖርበት አካባቢ በተለያዩ መድረኮች ላይ እየተገኘ ሙዚቃውን ይጫወታል። ታዲያ በእነዚህ መድረኮች በአማርኛ ሲያንጎራጉር የሰሙ ታዳሚዎቹ አማርኛ በመናገሩም ይደነቃሉ።

በተደጋጋሚም ''ይህ ፈረንጅ ከየት አመጣው ይሄን አማርኛ'' ሲሉ ሰምቷቸው ያውቃል።

ለኢትዮጵያ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ከመናገር ወደኋላ የማይለው ሊዮ ''ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝ ግንኙነት መቼም አይቋረጥም። ኢትዮጵያ መኖር በጣም ብወድም እንኳን አንድ ቦታ ግን ስላላደኩኝ በየተወሰነ ጊዜ መቀየር ግድ ይለኛል'' ይላል።

ከልጅ ሊዮ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለማዳምጥ ከታች ያለውን ቪድዮ ያጫውቱ።