እስራኤል ስደተኞች የማስወጣት ዕቅዷን ሰረዘች

African asylum seekers, mostly from Eritrea, protest in Jerusalem, Israel. File photo

እስራኤል ስደተኞችን ከሃገሯ የማስወጣቱን መርሃ ግብር እንዳቋረጠች የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ቢሮ አስታወቀ።

ውሳኔው የተላለፈው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በተደረገ ስምምነት መሆኑም ይፋ ሆኗል።

16 ሺህ ያህል ስደተኞች በጀርመን፣ጣልያንና ካናዳ እንደሚጠለሉ እንዲሁም 18 ሺህ ያህል ደግሞ በእስራኤል ቋሚ የነዋሪነት መታወቂያ እንደሚሰጣቸው ተነግሯል።

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እሁድ ዕለት ሊፈፀም እቅድ ተይዞለት የነበረው አፍሪካውያን ስደተኞችን የማበራር መርሃ ግብር ለተወሰኑ ቀናት እንዲገታ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ስደተኞቹን ይቀበላሉ ተብለው የታሰቡት ሃገራት ኡጋንዳና ሩዋንዳ ሲሆኑ ይህንን ሃሳብ የተቃውሙ በእስራኤል ያሉ የመብት ተሟጋቾች አለመስማማታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ሲገልፁ ቆይተዋል።

አዲሱ ዕቅድ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ሥራ ላይ ይውላል። የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ መሥሪያ ቤት ይህን ስምምነት 'ታይቶ የማይታወቅ' በማለት ገልፆታል።

በእስራኤል ከሚገኙ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች መካከል አብዛኛዎቹ የዜጎችን መብት በመጣስ በተባበሩት መንግሥታት የምትወቀሰው የኤርትራና በጦርነት ከተናወጠችው ሱዳን ዜጎች ናቸው።

ስደተኞቹ በሃገራቸው ከነበረው አደጋ ህይወታቸውን ለማትረፍ እንደተሰደዱ ሲናገሩ የእስራኤል መንግሥት ግን አብዛኞቹ ጥገኝነት የጠየቁበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነው በማለት ይከራከራል።