አዲስ የሞባይል ቀፎ በኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ላይ ለማሰመዝገብ ማወቅ ያለብዎት

የኢትዮ ቴሌኮም ሎጎ Image copyright Ethio telecom

ኢትዮ ቴሌኮም ከመስከረም 2009 ዓም ጀምሮ የደንበኞችን የሞባይል ቀፎ የመመዝገብ (Equipment Identity Registration System - EIRS) አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል።

ይህም ምዝገባ ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት፤ ደህንነትን ማስጠበቅ እና ለአገሪቱ ገቢ ማስገባትን ዓላማ ያደረገ እንደነበር ድርጅቱ አስታውቆ ነበር።

በተጨማሪም በሕገወጥ መንገድ የገቡና ጥራታቸው ድርጅቱ የሚያቀርበውን አገልግሎት የማይመጥኑ ስልኮችን ለመከላከል ታስቦ የተጀመረ መሆኑንም ጨምሮ ገልጾ ነበር።

በአሁኑ ሰዓትም አዲስ ቀፎ ገዝቶ ለመጠቀም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቅ በኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ላይ መሥራት የማይችሉ ስልኮችን ተታለው በመግዛት ለኪሳራ እየተዳረጉ እንደሆነ ተጠቃሚዎች ያማርራሉ።

ይህን ለማሰቀረት ምንድነው መደረግ ያለበት ብለን የኦሮሞ አይሲቲ መስራችና ዳይሬክተር የሆነውን አቶ አብዲሳ በንጫን ጠይቀን ነበር።

አዲሰ ቀፎ ሲገዛ ምን መደረግ አለበት?

አንድ ስልክ ሲመረት 15 አሃዝ ያሉት አይኤምኢአይ('IMEI') ሚስጥር ቁጥር ጋር ነው የሚሠራው።

ይህን አይኤምኢአይ('IMEI) ቁጥር ለማወቅም *#06# በመደወል ማወቅ ይቻላል።

Image copyright Getty Images

ሆኖም አስመስለው የሚመረቱ ቀፎዎቸ የትክክለኞቹን ስልኮች መለያ ቁጥር በማስመሰል ሊሠሩ ስለሚችሉ በኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ላይ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ ማለት ነው።

ድርጅቱ ገና ይህን አገልግሎት ሲጀምር ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ በማስመሰል የተሠሩ የሞባይል ቀፎዎች አገልግሎት መዋላቸውን ለይቻለሁ ብሎ ነበር።

በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም እነዚሀ ስልኮች ከአገልግሎት ዉጭ እንደሚሆኑ እና ደንበኞቹም በቶሎ እንዲያሰመዘግቡ አሰታዉቋል።

ስለዚህ አዲሰ ቀፎ ሲገዛ አስመስለው የተሠሩ አለመሆናቸውን በማወቅ ካልተገባ ኪሳራ መዳን እንደሚቻል ባለሙያው ያስረዳሉ።

ትክክለኛዎቹን ቀፎዎች ለማወቅ እነዚህን ቅደም ተከተሎች ይከተሉ

1- ሊገዙት ያሰቡት ቀፎ ውስጥ ሲም ካርድ ያስገቡ

2- *868# በመተየብ ይደዉሉ። ከዚያም 3 አማራጮች ይመጣሉ

እነዚህም አማራጮች፡

1- ፎን አንሎክ( Phone Unlock)

2- ስዊች አንሎክ (Switch Unlock)

3-ቼክ ስታተስ (Check Status) የሚሉ ናቸው።

በመጣልን የቁጥር መጻፍያ ቦታ ላይ 3ኛውን ቼክ ስታተስ (Check Status) የሚለውን በማሰገባት መላክ ወይም ሴንድ የሚለውን (SEND) ቁልፍ መጫን። ከዚያም 2 አማራጮች ይመጣሉ።

እነዚህም አማራጮች፡

1- ባይ አይኤምኢአይ (By IMEI)

2-ባይ ፎን ነምበር (By Phone number) የሚሉ ናቸው።

1- ባይ አይኤምኢአይ (By IMEI) የሚለውን በማስገባት ስንልከው ወይም ሴንድ (SEND) ስንለው ወዲያውኑ አይኤምኢአይ ቁጥር አስገቡ (Enter IMEI number) የሚል መልዕክት ይመጣል።

ከዚያም በማስገባት *#06# የምናገኘውን የ አይኤምኢአይ 'IMEI' ሚስጥር ቁጥር አስገብተን መልእክቱን መላክ ወይም ሴንድ (SEND) እንለዋለን።

ከዚህ በኋላ ወዲያዉኑ በኢትዮ-ቴሌኮም ኔትዎርክ ላይ የሚሠራና የማይሠራ ቀፎ መሆኑን ያውቃሉ።

መደረግ የሌለባቸው

ከላይ በተጠቀሱት መሠረት ትክክለኛውን ስልክ ማግኘት ካልቻሉ፤ ቀፎው አዲስ ነውና ገና ከእሽጉ ስላልተፈታ ነው ተብሎ መገዛት እንደለሌለበት ባለሙያው ይመክራሉ።

እንዲሁም በተጨማሪ ሳይከፈት በፊት ለ 3 ሰዓታት ቻርጅ መደረግ አለበት በማለት ሻጮች ሊሸጡ ቢሞክሩ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችልም ተናግረዋል።

ከውጭ አገር የሚመጡ ስልኮችን አስመልክቶ

ከውጭ አገር የሚመጡ ስልኮችን በተመለከተ ስልኩን ያመጣው ሰው ካለ አንድ ስልክ በነፃ ማሰመዝገብ የሚችል ሲሆን፤ ከዚያ በላይ ቁጥር ላላቸው ቀፎዎች 45% ግብር በመክፈል ማስመዝገብ የሚቻል መሆኑን ነው የተገለጸው።