የሞያሌ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ ከምን ደረሰ?

ከቻሙክ ቀበሌ ተፈናቀሉ ሰዎች የሰሩት የላስቲክ ቤቶች
የምስሉ መግለጫ,

ከቻሙክ ቀበሌ ተፈናቀሉ ሰዎች የሰሩት የላስቲክ ቤቶች

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሞያሌ በመንግስት ወታደሮች በተፈፀመ ጥቃት ሸሽተው የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች የተመለሱ ሲሆን አሁንም በርካቶች በኬንያ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ተፈፀመ በተባለ ጥቃት 10 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ 'ለደህንነታችን ሰግተናል ብለው ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ መሸሻቸው ይታወሳል።

ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከሸሹት መካከል ወ/ሮ አይሻ ጎሊቱ አንዷ ናቸው።

ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት 11 ልጆቻቸውን ይዘው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ወደ ኬኒያ ሸሽተው የነበረ ሲሆን አሁን ግን ወደ ቀያቸው ልጆቻቸውን ይዘው ተመልሰዋል።

"ሁሉም ባይሆን የተመለሱ ሰዎች አሉ። እኛ ከተመለስን አንድ ሳምንት አልፎናል። የዛን ዕለት ግለሰቦችን የገደሉ ሰዎች ታስረዋል ተብለዋል።አሁን በሰላም እያደርን ነው፤ የተኩስ ድምፅም አይሰማም።" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ሶመሬ ጊዜያዊ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይገኛሉ።

በጣቢያው የወርልደ ቪዥን ጊዜያዊ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ደንከን ኦዲዮ በበኩላቸው

"ሁኔታዎች ብዙም አልተቀየሩም ምንም እንኳን ድንበር ተሻግረው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም። ስደተኞችን መዝግበን ይዘናል። እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ የሉም።" ብለዋል።

በአካባቢው የሚገኘው ጋዜጠኛ ካሲም ዋቆ ለቢቢሲ እንደገለፀው የመርሰቤት ግዛት ስደተኞቹን መዝግቦ ካኩማ ወደሚባል የስደተኞች ጣቢያ ሊያሸጋግር ነው።

የመርሰቤት ግዛት አስተዳዳሪን ያነጋገረውም ካሲም እንደገለፀው "በቀጣይ ሁለት ሳምንታት መንግሥት የስደተኞችን አሻራ ጨምሮ መረጃቸውን ከሰበሰበ በኋላ እንደ ስደተኛ አድርጎ ይመዘግባቸዋል።

ለመመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይም እርምጃ ይወስዳል። የተመዘገቡ ስደተኞች ወደ ካኩማ የስደተኞች ጣቢያ ይላካሉ" ብሏል።