በመቅደላ ውጊያ ከኢትዯጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት ለመለሱ ነው

V&A Museum, Maqdala 1868 display: Crown, gold and gilded copper with glass beads, pigment and fabric, made in Ethiopia, 1600-1850

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ከ150 ዓመታት በፊት በነበረው የመቅደላ ውጊያ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው የተወሰዱ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ዘውድ፣ የሰርግ ቀሚስና የወርቅ ዋንጫዎችን በውሰት ሊመልስ ነው።

ከእነዚህ ቅርሶች መካከል የተወሰኑት እንደ አውሮፓውያኑ በ1868 የተካሄደው የመቅደላ ጦርነት አመታዊ በአል ሲዘከር ለእይታ መቅረባቸው ጥያቄዎችን አስነስቷል።

የእንግሊዝ ሃይል ቅርሶቹን ከመቅደላ ለመውሰድ 15 ዝሆኖችንና 200 በቅሎዎችን ለማጓጓዣነት ተጠቅመው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

የምስሉ መግለጫ,

በ1860 የተሰራው ይህ የሰርግ ቀሚስ የንግስት ጥሩነሽ እንደሆነ ይታመናል።

በ2008 ኢትዮጵያ ከመቅደላ የተዘረፉና በሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ቅርሶቿ እንዲመለሱላት ለተለያዩ የእንግሊዝ ቅርስ ተቋማት ጥያቄ አቅርባ ነበር።

የቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ዳይሬክተር ትሪስትራም ሀንት ግን ቅርሶቹ የእንግሊዝ ሆነው እንደሚቀጥሉ ነገር ግን ለረዥም ጊዜ መቆየት ይችሉ ዘንድ በውሰት ወይም በብድር መልክ ለኢትዮጵያ ሊሰጡ እንደሚችሉ አስታወቁ።

መቅደላ 1868

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

  • በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቴዎድሮስ ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት በመፍጠር አቢሲኒያን ለማዘመን ወሰኑ
  • ነገር ግን የወታደራዊ ድጋፍ ጥያቄያቸው በእንግሊዝ ችላ በመባሉ የአገራቱ ግንኙነት ሻከረ።
  • ለዚህ በምላሹም ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ቆንስላና ሌሎች የውጭ ሃገር ዜጎችን አሰሩ።
  • ይህን ተከትሎ እንግሊዝ ወደ መቅደላው የንጉሱ ቤተ መንግስት ጦር ሃይል ላከች።
  • በእንግሊዞች እጅ አልወድቅም በማለት ቴዎድሮስ ራሳቸውን አጠፉ።
  • የእንግሊዝ ጦርም ውድ ብራናዎችን፣አክሊሎች፣መስቀል፣የወርቅ ዋንጫዎችን፣የንጉሳዊያንና የቤተ ክርስትያን ቁሳቁሶችን ጋሻና የመሳሰሉትን ዘርፈው ወሰዱ።
  • በጊዜው የንጉሱ የሰባት ዓመት ልጅም ወደ እንግሊዝ ተወስዶ በራግቢ ትምህርት ቤት እንዲማር ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

  • ልጃቸው በ18 ዓመቱ በሳንባ በሽታ ሲሞት በዊንድሶር ቤተመንግስት ተቀበረ።
  • የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም የወርቅ አክሊልና ዋንጫ አስቀምጧል።
  • ከመቅደላ የተዘረፉት ሌሎቹ ቅርሶች ከግለሰቦች ለሙዚየሙ በስጦታ የተበረከቱ ናቸው።

የሙዚየሙ ዳይሬክተር ሚስተር ሃንት ለአንድ የኪነጥበብ ጋዜጣ እንደገለፁት ሙዚየሙ ቅርሶቹን ለኢትዮጵያ ማዋስ እንደሚፈልግ በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ ሃይለሚካኤል አበራ አፈወርቅም "ከሙዚየሙ ጋር በተፈጠረው አጋርነት ተደስተናል ለጋራ ጥቅማችን አብሮ የመስራት ፍላጎትም አለን"ሲሉ ለጋርዲያን ተናግረዋል።

ሙዚየሙ እንዳስታወቀው ለዕይታ የቀረቡት እነዚህ ቅርሶች ታዳሚዎች የዕጅ ጥበብን ውበትና የብረታ ብረት ስራና የጥልፍ ዲዛይን ረቂቅነትን እንዲሁም ከቅርሶቹ ጋር የተያያዘውን አወዛጋቢ ታሪክ እንዲያስተውሉ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

የምስሉ መግለጫ,

የንግስት ጥሩነሽ የአንገት ጌጥና ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሰራ ዋንጫም ለእይታ ይቀርባሉ።

ለዘመናዊ ፎቶግራፍ መሰረት ነበሩ የተባሉ የጦር የእንግሊዝ ጦር ሃይል ፎቶግራፎችም ለእይታ እንደሚቀርቡም ሙዚየሙ አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, V&A Museum

የምስሉ መግለጫ,

ይህ በመቅደላ የሚገኝ ቤተክርስትያን ፎቶ የተነሳው በእንግሊዝ ንጉሳዊ መሃንዲሶች ነው።