ዊኒ ማንዴላ -አልበገር ባይ እናት

A picture taken on April 13, 1986 shows Winnie Madikizela-Mandela, then-wife of South African president Nelson Mandela, addressing a meeting in Kagiso township.

ባህላዊ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ ህዝብና ደጋፊዎቻቸው በእንከን የለሽ ሴትነታቸው እንዲታወሱ ይፈልጋሉ።በተቃራኒው በተለይም የነጭ የበላይነት ተጠብቆ እንዲቆይ የታገሉ ዊኒ በቀውስ ፈጣሪነትና በጥፋት የተተበተቡ በመሆናቸው እንዲታወሱ ይፈልጋሉ።

ነገር ግን እውነት ዊኒ ማንዴላ ማን እንደነበሩ መረዳት የሚፈልግ ለዓመታት ወደ ኋላ ሄዶ በአፓርታይድ ስርዓት ያለፉበትን ስቃይና ውርደት መመልከት ይኖርበታል።

ዊኒ የነፃነት ታጋይ፣ ቀጭ ብለው በፌስቡክ ወይም በትዊተር ሳይሆን በአካል አፓርታይድን የታገሉ አብዮተኛ ነበሩ።

የሁለት ልጆቿ አባት ኔልሰን ማንዴላ እንደ አውሮፓውያኑ በ1962 ታስረው እድሜ ልክ ሲፈረድባቸው ልጆቻቸውን ለብቻቸው የማሳደግ ሃላፊነት ወድቆባቸው ነበር።

የስቃይ ጊዜ

በአውሮፓውያኑ 1969 ለ491 ቀናት ለብቻቸው ተነጥለው እንዲታሰሩ ተደርጓል።ያኔ በወር አበባቸው ጊዜ እንኳን ንፅህና መጠበቂያ ማግኘት ለዊኒ የሚታሰብ አልነበረም።

የማሰቃያ ክፍሉ ለክፍላቸው ቅርብ ነበርና የእስረኞች የስቃይ ድምፆች በህሊናቸው ቀርተዋል።

"የእስረኛ ቁጥር 1323/69"የሚለው የእለት ማስታወሻቸው "491 ቀናት" በሚል ርእስ በመፅሃፍ መልክ ታትሞ ነበር።ብዙ የፀረ አፓርታይድ ታጋዮች እስር ቤት ሲሰቃዩና ብዙዎችም ሸሽተው ካገር ሲወጡ ዊኒ ትግሉን የወከሉ ብቸኛዋ ሰው አልነበሩም።ይልቁንም ራሳቸው ትግሉን ነበሩ ቢባል ይቀላል።

ዊኒ ሲዞሩ የትግል ግንባሩም ይዞር ነበር።በማንዴላ ወህኒ መውረድ የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት ሳይሆን ዊኒ በራሳቸው ቦታና አቅም ትግሉን አንቀሳቅሰዋል።

የአፓርታይድ ስርአት ሊቆጣጠራቸው የማይቻለው ሃይለኛ ሴት መሆናቸውን ሲረዳ በጆሃንስበርግ ከሚገኘው ቤታቸው መኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሎ የነጮች የበላይነት ወደ ነገሰበት የብራንደፎርድ ገጠር ከተማ አሰደዳቸው።

በዚህ ቤታቸው ምንም አይነት እንግዳ እንዲያስተናግዱ አይፈቀድም ነበር ይልቁንም የአፓርታይድ ስርአት አስከፊነትን ለአለም ለመንገር በየቀኑ ስልክ ለመደወል በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፖስታ ቤት ይሄዱ ነበር።

ውብና ግርማ ሞገስ የተላበሱ

ስለ ዊኒ አሉታዊ አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ ዊኒ ያለፉበትን አስከፊ በዘረኝነትና ጾታን መሰረት ያደረገ መድሎ የተወሳሰበ ህይወት የረሱ ናቸው።

ምንም እንኳ ባህሪያቸውና መንፈሰ ጠንካራነታቸው ይህ አስከፊ የህይወት እጣ እንዳይሰብራቸው ቢያደርግም።

ዊኒ ፍርሃት የሚባል ነገር የሌለባቸው ታጋይ ብቻ አልነበሩም።በጣም ቆንጆም ነበሩ።የተጋፈጣቸው የአፓርታይድ ፖሊሶች እንኳ ሊረሱት የማይችሉት ፈገግታና ግርማ ዊኒ ነበራቸው ።

ነገር ግን ዊኒ እንደ ሰው ድክመት ነበረባቸው።

በማጭበርበርና በጠለፋ በመተባበር ተከሰው ነበር።

ፀረ አፓርታይድ ትግሉን የከዱ እሳት የተለኮሰ ጎማ እንገታቸው ላይ ገብቶ በሞት እንዲቀጡ መደገፋቸውም ዊኒን ከበርካታ የትግል ጓዶቻቸው ጋር ሆድና ጀርባ አድርጓቸው ነበር።

'የአፓርታይድ አሻራ'

የዊኒን ህልፈት ተከትሎ የፀረ አፓርታይድ ትግል አቀንቃኙና ተቃዋሚው ሞሲዋ ሊኮታ "በኦፓርታይድ ዘመን ምንም ያላደረጉ ምንም ስህተት አልሰሩም" በማለት ዊኒ ስርአቱን ለመጣል ብዙ ዋጋ እንደከፈሉ ተናግረዋል።

ያለፉበት አስቸጋሪ መንገድ ዊኒን ለተለያዩ የስነ ልቦና ጫናዎች አጋልጠዋቸው ነበር።

1936: ዊኒ በምስራቃዊ ኬፕ ትራንስኪ ተወለዱ

1958: ኔልሰን ማንዴላን አገቡ

1969: በፀረ አፓርታይድ ትግል ለአንድ አመት ተኩል ታሰሩ

1976: በአፓርታይድ ስርአት ባለስልጣናት ወደ ገጠር ተላኩ

1991: በጠለፋ ወንጀል ተፈረደባቸው

1994: የፓርላማ አባል ሆነው ተመረጡ፣እስከ እለተ ሞታቸው የፓርላማ አባል ነበሩ።

1996: ከኔልሰን ማንዴላ ተፋቱ

2003: በማጭበርበር ተፈረደባቸው

ከ1970ዎቹ ጀምሮ ዊኒን የምታውቃቸው ፀሃፊዋ ቸሃርልን ስሚዝ የፌስ ቡክ ገጿ ላይ

"ዊኒ የአፓርታይድ ስርአትን አሳዛኝ እውነታ የረሳ ሃገር ህሊና ናት።ሞታ እንኳ ምን ያህል እንደተሰቃየችና እንደተሰበረች አይረዱም" በማለት አስፍረዋል።

"ደቡብ አፍሪካ ዘሬ በአለም ላይ ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ የሚፈፀምባት አገር ነች።በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተሰበሩና የተጎዱ ዜጎች አሉባት ይህ ደግሞ የአፓርታይድ አሻራ ነው።ዊኒ ላበረከተችው አስተዋፅኦ ዋጋ መስጠት የምንችለው የተሰበሩና የቆሰሉ ሰዎችን በማስታወስና በማከም ነውም"ብለዋል።