በምድር ባቡር ግንባታው የተፈናቀሉ የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች ካሳ አልተከፈለንም አሉ

አዲሱ የሚሰራው የባቡር መንገድ ካርታ

ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክፍል ከመሃል አገር እና ከወደብ ጋር ማገናኘትን ዓላማ ያደረጉት የአዋሽ - ኮምቦልቻ - ወልዲያ ሃራ ገበያ እና የወልዲያ ሃራ ገበያ - መቐለ የባቡር መስመሮች ዝርጋታቸው ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል።

ከአዋሽ እስከ ወልዲያ ሃራ ገበያ 398 ኪ.ሜ እርዝማኔ ያለው ሁለተኛው የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነው ከመቐለ እስከ ወልዲያ ሃራ ገበያ ድረስ 216 ኪ.ሜ እርዝማኔ አለው።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ ያለውን የባቡር መስመር ዝርጋታ 95% አጠናቅቆ የሙከራ ጉዞ ለመጀመር የኤሌክትሪክ አቅርቦትን እየጠበቀ እንደሆነ ይገልፃል።

ግንባታው ማሳዎቻቸውን የወሰደባቸው በሰሜን ወሎ ዞን ልዩ ልዩ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ላለፉት ሦስት ዓመታት ካሳ ያለማግኘታቸውን ይህም ህይወታቸውን ፈታኝ እንዳደረገባቸው ይገልፃሉ።

ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር በካሳ መልኩ መክፈሉን የቀረውም ከመረጃ መጓደል እና ተገቢውን ማጣራት ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው ይላል።

በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ዘገየ መርሴ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ እና ቆቦ ወረዳ ዜሮ አራት ጃሮታ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

ለወትሮው በማሳቸው ላይ ልዩ ልዩ የእህል ዘሮችን እንዲሁም አትክልትን በማብቀል ስድስት አባላት ያሉትን ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

እርሻው የሚገኝበት አካባቢ ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮበት በዓመት ሦስት ጊዜ ያመርት የነበረ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ዘገየ በ2007 ዓ.ም የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ የባቡር መስመር ግንባታ በተጀመረበት ወቅት ይተዳደሩበት የነበረውን መሬት ካጡ በኋላ ሌሎች መሬት እየተከራዩ ለማረስ እንዲሁም የቆጠቡትን ለመጠቀም መገዳደቸውን ይገልፃሉ።

"በእጅጉ ከፍቶናል። ብንጮህ ብንጮህ አድማጭ አጥተን፤ በጣም ተቸግረን ነው ያለነው።"

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የገንዘብ ካሳ እንደሚሰጣቸው ቃል ቢገባላቸውም፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ኪሳቸው የገባ ገንዘብ ባይኖርም ጥያቄ ከማቅረብ ግን ቦዝነው እንደማያውቁ ጨምረው ያስረዳሉ።

አቶ ዘገየ በቀበሌያቸው ክፍያ ካልተሰጣቸው ስልሳ ስድስት ሰዎች መካከል አንደኛው ናቸው። ከ10200 ካሬ ሜትር በላይ መሬት እንደተወሰደባቸው የሚናገሩት አቶ ዘገየ በካሬ 239 ብር እንደሚከፈላቸው ተነግሯቸው መፈረማቸውን ለቢቢሲ ይገልፃሉ።

የጉባ ላፍቶ ወረዳ ዜሮ ስድስት ቀበሌ ምክትል ሊቀ መንበር እና አርሶ አደር አቶ አዲሴ አለሙ ነጋሴም ከሶስት ዓመት በፊት ለባቡሩ ግንባታ ተብሎ መሬታቸው የተወሰደ ሲሆን እስካሁን ድረስ ካሳ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ።

ምንም እንኳን የመሬቱን ልኬታ በሄክታር እንደማያውቁ አቶ አዲሴ ቢናገሩም በ1983 ዓ.ም በላጤነት መሬቱ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።

መሬቱ ከተመዘገበበት ከ2006 ጀምሮ የአስር ዓመት ካሳ ክፍያ ይሰጣችኋል ተብለው ቃል ቢገባላቸውም ዓመት ዓመታትን እየቆጠረ እስካሁን ድረስ ውጤት እንዳላዩ ይገልፃሉ።

በቅርብም ቀናት እሳቸውን ጨምሮ 110 ለሚሆኑ አባወራዎች ብራቸው ተለቆ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገብቶላችኋል ተብሎ ቢነገራቸውም ለትራንስፖርት ገንዘብ ከመጨረስ ውጭ ምንም የተፈየደላቸው ነገር እንደሌለ ይገልፃሉ።

አቶ አዲሴ በቀበሌያቸው ምክትል ሊቀ-መንበር ቢሆኑም ምንም መረጃ እንደሌላቸውና ብሶትና ለቅሶ በአካባቢው እየተባባሰ እንደመጣ ገልፀዋል።

"አስር ቤተሰብ ነው የማስተዳድረው፤ ነገር ግን በባለፉት ሶስት ዓመታት የሰው መሬት እየተኮናተርኩ ተቸግሬ ነው ያለሁት። ይመለለከተዋል ለሚለው ወረዳ ሁሉ እያመለከትን ነው። ነገር ግን በተደጋጋሚ ቃል ቢገባልንም ከቃል የዘለለ ነገር የለም" በማለት በምሬት ይናገራሉ።

የባቡር መንገዱ ግንባታ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ በቀበሌው ለሚኖሩ ከመቶ በላይ መሬት ለተወሰደባቸው ገበሬዎች የካሳ ክፍያ የተፈፀመ ቢሆንም የቀሪዎቹ ግን እስካሁን ያልተፈፀመው "በአጋጣሚ" ብቻ እንደሆነ አቶ ዘገየ ያምናሉ።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተረፈ ግን በአጋጣሚ የሚከናወን ምንም ነገር እንደሌለ ነው የሚገልፁት። "መጣራት ያለበት ነገር ካለ ይጣራል፤ ለምሳሌ መጠን። ገንዘብ ስለሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል" ይላሉ።

ፕሮጄክቱ ከተጀመረ አንስቶ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር የግምት ካሳ ኮርፖሬሽኑ ለአርሶ አደሮች መክፈሉ የሚያወሱት አቶ ደረጀ ጉዳዩን ለሕዝብ ተወካዮች ጭምር ማስረዳታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ህግን ተከትለው እየሰሩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ደረጀ መሬታቸው ለተወሰደባበቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የመሬት ግምታቸው ስሌት እንደሚሰጣቸው ይናገራሉ። አቶ ደረጀ እንደሚናገሩት ይህ የመሬት ግምት ስሌት የሚሰራው የመሬቱን ምርታማነት፣ በዓመት የሚያመርቱበት ጊዜ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

ካሳው መመሪያውን በመከተል ወደ ኋላ 10 ዓመትን የሚያይ እንደሆነ የሚገልፁት አቶ ደረጀ ለምሳሌነትም በዓመት 30 ኩንታል ጤፍ የሚያመርት አንድ አርሶ አደር የ30 ኩንታል ጤፍ ግምት ዋጋ በአስር ዓመት ተባዝቶ የሚሰጠው ድምር ነው ይላሉ።

ወቅታዊ ከሆኑ ምርቶች ውጭ ቋሚ ዛፎች፤ አትክልቶችና ፍራፍሬዎችም በተለየ መንገድ ግምታቸው ይሰላል። ይህንን ግምት የሚያሰላ ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣው የወረዳው ገማች ኮሚቴ እንደተቋቋመምም አቶ ደረጀ ይናገራሉ።

ምንም እንኳን አቶ ደረጀ ብዙ አርሶ አደሮች ካሳ እንደተከፈላቸውና ቀሪዎቹ ትንሽ እንደሆነ ቢገልፁም ያናገርናቸው አርሶ አደሮች በዚህ ሀሳብ አይስማሙም። ለምንስ ይህን ያህል ረዥም ጊዜ ወሰደም ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ደረጀ ሲመልሱ የማጣራት ስራው ሂደት እንደሆነ ይናገራሉ።

የምርት ዓይነት፣ የመሬቱ መጠን እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን አካቶ የሰነድ መረዎች ካለቁ በኋላ መሆኑን ይናገራሉ። " የአያት ስም የሌለው ሰነድ ይመጣል። የምርት ዓይነቱን በተሳሳተ መንገድ የሚያመጡ አሉ። ከዚህም በተጨማሪ የባቡሩ መስመር የማያልፍባቸው ካሳ የተከፈላቸው አሉ። ይህም ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘ ነው። " ይላሉ።

አዋሽ ሃራ ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ የሚገነባ ሲሆን 1.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለታል ከዚህ ውስጥ 15% በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ሲሆን ሌላው በብድር እንደሚሸፈን አቶ ደረጀ ያስረዳሉ።