የቤት ሰራተኞችን ለመላክ ከኩዌት ጋር ድርድር እንደሚያስፈልግ ኢትዮጵያ አስታወቀች

"የቤት ሰራተኞችን ለመላክ ከኩዌት ጋር ድርድር ያስፈልጋል" Image copyright AFP

በቤት ሰራተኝነት ወደ ተለያዩ አረብ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈፀመውን ከባድ አካላዊ ጥቃትና ሌሎች ችግሮችንም ተከትሎ መንግሥት በቤት ሰራተኝነት ወደእነዚህ ሃገራት የሚደረግ ጉዞን አግዶ ነበር።

አዲስ የውጭ ሃገር የሥራ ስምሪት አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግስት እገዳውን ማንሳቱ ይታወቃል።

የ29 ዓመቷ ፊሊፒናዊት በአሰሪዎቿ መገደሏን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ፊሊፒንስ ዜጎቿ ወደ ኩዌት ሄደው በቤት ሠራተኝነት እንዳይሰማሩ ህግ አውጥታለች።

ይህ ከተሰማ ሰዓታት በኋላ ነው የኩዌት ባለሥልጣናት ሃገሪቱ የገጠማትን የቤት ሠራተኛ እጥረት ለመቅረፍ ኢትዮጵያውያንን ለመቅጠር ዝግጁ መሆናቸውን ያስታወቁት።

ጉዳዩ የሚመለከተው የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ሃገር ስራ ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ብርሃኑ አበራ ግን የኩዌትን ፍላጎት በተመለከተ ጉዳዩ ገና ነው ይላሉ።

በቤት ሰራተኝነትና በተለያዩ የጉልበት ስራዎች የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚገኙባትና ቀደም ሲል በቅርቡም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከግዛቷ ጋር ካስወጣችው ሳውዲ አረብያ ጋር ስምምነት ተደርጓል።

በአዲሱ አዋጅ መሠረት የቤት ሰራተኞችን የመላክ ስምምነቱ ያለቀለት ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል የሚቀር ነገር እንዳለ አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ።

በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ነገሮች መዘግየታቸውንና ወደ ተግባር ለመግባት ስምምነቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቅ እንደሚጠበቅበትም ያስረዳሉ።

"ሰነዱ አሁን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሷል፤ አዋጁ ወደ ተግባር የሚገባው ስምምነቱ ሲፀድቅ ነው።" ይላሉ።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ከኩዌት ጋር የተፈራረመችው ሰነድ ቢኖርም አሁን ስምምነቱ መሻሻል እንደሚኖርበት አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ።

በዋነኛነትም ከኩዌት ጋር "የሁለትዮሽ ድርድር ያስፈልጋል" ይላሉ።።

በአሁኑ ወቅት በምዕራባዊ እስያና በምስራቅ አረብ መካከል በምትገኘው ኩዌት 15 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ ይገመታል።