ትንሳኤን "አድማቂ" ገጣሚያን

Image copyright Muluken Asrat
አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ወደቀኝ ገጣሚያኑ ኤፍሬም ስዩም፣ምልዕቲ ኪሮስ እና ደምሰው መርሻ

ሆሳህና ከሚሰኘው የቅድመ- ትንሳኤ እሁድ ጀምሮ፣ ዳግማይ ትንሳኤ እስከሚባለው ድህረ-ትንሳኤ እሁድ ድረስ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ያለው ጊዜ በፋሲካ በዓል ድባብ የደመቀ ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን በዓሉን ለማድመቅ፤ መንፈሳዊና ዓለማዊ የኪነጥበብ ስራዎችን ለታዳሚዎቻቸው በላይ በላዩ ይጋብዛሉ፡፡ ከስነ-ግጥም ግብዣዎች ውስጥ በትንሳኤ ሰሞን ተደጋግመው ከሚሰሙ ስራዎች መካከል የገጣሚ ኤፍሬም ስዩም "የጅራፍ ንቅሳት"፣ የገጣሚ ደምሰው መርሻ "የክርስቶስ ሀሙስ"፣ የገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ "የይሁዳ ሚስት'' ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

ገጣሚያኑ ዳቦ ባይቆረስም፣ በአደባባይ ባይታወጅም በዚህ ሰሞን ስራዎቻቸው ተደጋግመው መደመጣቸው 'ትንሳኤን አድማቂ' ገጣሚያን መሆናቸውን ግልጽ ያደረገው ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ገጣሚያኑን ከበዓላት ነጥለው ትንሳኤና ተዛማች ክንውኖቹ እንደምን የንሸጣ ምክንያት ሆናቸው?

"እኔን እንድጽፍ ያደረገኝ ትልቁ ሃሳብ የጌታችን መከራው፣የደረሰበት ስቃይ ነው፤» የሚለን ግጥምን ከሙዚቃ ጋር አስማምቶ በማስደመጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደበው ገጣሚ እና ደራሲ ኤፍሬም ስዩም ነው። በትንሳኤ ሰሞን ተደጋግሞ የሚደመጠውን "የጅራፍ ንቅሳት" የተሰኘ ግጥሙን መነሻ ሲያብራራም ፣ "በሱ ስቃይ እኛ ተፈውሰናል፤ ድነናል። ስለዚህ እኔ ልደሰት ነው የሚገባኝ፤ ይሄ ሁሉ መሰዋእት ለኔ ነው የተከፈለው። ያንዳንዱ ሰው ይሄን ደስታውን በተለያየ መንገድ በመዝሙር፤ በስዕል ይገልጻል። እኔ ደግሞ የምገለፅው በመጻፍ ነው፤"ይላል።

በራስ ሆቴል መድረክ ላይ ወር ጠብቆ በሚቀርበው ጦቢያ የግጥምን በጃዝ ድግስ ላይ የሚታወቀውና እና በቅርቡም 'ያልታየው ተውኔት' የተሰኘ የግጥም ቅጂውን ያስደመጠን ደምሰው መርሻ በበኩሉ፣ እንዴት ትንሳኤ የስንኞቹ መነሻ እንደሆነው ሲያስረዳ ፣ «ከሞት በኃላ የሚመጣን ህይወት ማሰብ፤ ከሽንፈት በሁዋላ የሚመጣን ድል ፤ ከውድቀት በኃላ መነሳትን የመሳሰሉ ብዙ ነገሮችን ያመለክታል።ይህ ክስተት የሰው ልጅ አዲስ የድህነት መንገድ ያግኘበት እና ሞት የተሸነፈበት በመሆኑ ነው፤"ይላል።

በደምሰው የግጥም 'አልበም' ውስጥ የተካተተው ‹‹የክርስቶስ ሀሙስ ›› እየሱስ ክርስቶስ ከደቀመዛሙርቱ ጋር በተጋራው የመጨረሻ እራት ላይ በአዕምሮው ይብሰለሰሉ የነበሩ ጉዳዮችን ያስቃኛል፡፡

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ትንሳኤን "አድማቂ" ገጣሚያን- ደምስ መርሻ

"ልቤን ፍርሃት ናጠው ሲመጣ ሰዓቱ፣

ሊፈጸም ነው መሰል የመጻፍ ትንቢቱ፣

ጭፍሮቼን አየሁኝ፣

የማውቃው መልካቸው ለአሁን የተረሳኝ፣

ማን ይሁን ባለንጀር፣አሳልፎ ሰጪ ዛሬስ የሚስመኝ።"

እያለ ይወርዳል -የደምሰው ግጥም፡፡

ደምሰው በቅዱሳን መጽሃፍት ላይ በተጠቀሰ ክንውን ላይ የራሱን የገጣሚነት ዐይነ-ህሊና (Imagination) ጨምሮ ነው የሚተርክልን፡፡ዐይነ ህሊናን በመጠቀም ጉዳይ ደምሰው ብቸኛ አይደለም። ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ ኪናዊ ለዛ ለማላበስ እንደተደረገ ጥረት ትቆጥረዋለች-በምትታወቅበት "የይሁዳ ሚስት'' ግጥም ውስጥም ተጠቅመዋለች፡፡

"በኔ ግጥም ውስጥ ያለው ታሪክ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ አይደለም፡፡የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብዙ መጽሃፍትና አንድምታዎች አሏት-የኔ የግጥም ማጠንጠኛም እኒህን መጽሃፍት መሰረት ያደረጉ አስተምህሮቶች ናቸው፤›› ስትል የምታስረዳው ምልኢቲ በግጥሟ ዐይነ -ህሊናን እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ለማስማማት ያለውን የቤት ስራም ታጋራለች፣"እንደሚታወቀው የይሁዳ ሚስት የሚል የስቅለት ግጥም ነው እኔ ያለኝ፡፡ስለ ይሁዳ ቀደም ብሎ የነበረውንና በቤተክርስቲያን ዘንድ ሲነገር የነበረውን ታሪክ ነው መነሻ ያደረግኩት፡፡ ግጥሙን ከመጻፌ በፊት የአስራ ሁለቱን ሀዋሪያት የመጀመሪያ ስራቸውን ለመፈለግ ጥረት አድርጌያለሁ፣ እሱም ጊዜ ፈጅቶብኛል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የእኔ ባለታሪክ ይሁዳ የመጀመሪያ ስራው ወታደርነት እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ግጥሙ የተጻፈው በይሁዳ ሚስት (እናት) ምናብ ውስጥ ራሴን በማስቀመጥ ነው፣ እሷኑ ሆኜ ፤" በማለት ታክላለች።

ዓለማዊ አረዳድን እና መንፈሳዊ ሀሳቦችን ማስማማት የገጣሚያኑ የእጅ አዙር ፈተና መሆኑ አይካድም። እንዲህ ባለው ወቅትስ ገጣሚያኑ ምን ያስቀድማሉ?

"አንድ ሃሳብ ወደ ጽሁፍ ሲቀየር በራሱ መንፈሳዊ ነው ? ሚል ጥያቄ በግሌ አለኝ ፣" የሚለው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም ፣''ስለ ክርስቶስ ስንናገር ስለ እናት ፍቅር ተናግረናል፤ ስለ ይሁዳ ክህደት ተናግረናል፤ ለሰው ልጆች ስላለው ጥልቅ ፍቅር ተናግረናል።ምናልባት መነሻ ሃሳባችን ስጋ ለበስ ወይም ዓለማዊ ሊሆን ይችላል እንጂ በዛ ውስጥ የምንናገራቸው ነገሮች ጥልቅ የሆነውን መነካት መግለጫ ነው፤" ይላል።

ገጣሚ ደምሰው መርሻ በበኩሉ የማስማማት ሂደቱ በግጥሙ ጥንስስ ወቅት መታሰብ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ያምናል ፣" ከባዱ ነገር መጀመሪያ ሃሳቡን የቱ ጋር እንደምታስቀምጠው መወሰኑ ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁሉን ነገር ግጥም ልታደርገው አትችልም። ግን አንድን ሃሳብ ወደ ግጥም ስትቀይረው እዚህ ጋር መልእክቱ ይሄ ነው፤ የተመሰለው በህይወት ነው፤ በድህነት ነው ብሎ ማስቀመጥ ያሰፈልጋል። ስለዚህ ነገሮች ሁሉ የጋራ መግባቢያቸውን መፈለግ ነው ዋናው ፣እንጂ ከዛ በሁዋላ ብዙ አይከብድም፤'' በማለት እይታውን አካፍሎናል።

ገጣሚያኑ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓል በሆነው የትንሳኤ በዓል ሰሞን ግጥሞቻቸው ይደጋገሙ እንጂ ፣በሌሎች ዓለማዊ ግጥሞቻቸው ያፈሯቸው የሌላ ዕምነት ተከታዮች አሏቸው።መንፈሳዊ ትርክት ላይ መሰረት አድርገው የተፃፉ ስራዎቻቸውን እኒህ ተከታዮቻቸው በምን አግባብ እንዲረዱላቸው ፈልገው ይሆን?

"ቅዱስ ቁርአንም ሆን መጽሃፍ ቅዱስ ይሁን አንዳንዴ የተነሳህበትን መንገድ በአግባቡ የምትገልጸው ከሆነ ከአድማጮችህ ጋር አትጠፋፋም። ብዙዎቹ ሃሳቦች ሀይማኖትን አይደለም የሚሰብኩት፤ የተለያዩ ሃሳቦችንና ፍልስፍናዎችን እንጂ፤" ይላል ገጣሚ ደምሰው መርሻ ነው።ገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ በበኩሏ ከሃይማኖቱ ተከታዮች ውጪ ያሉ አድማጮች ሊገጥማቸው የሚችለውን ያለመረዳት ችግር ትቀበላለች ፣

"ለኦሮቶዶክስ አማኞች የኔ ሀሳብ አዲስ አይደለም፣ ለመቀበልም አይቸግራቸውም ብዬ አስባለሁ፡፡የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ግን ግጥሙን እንደ ግጥም ለመረዳት እኒህን መጽሃፍት ትንሽ ማገላበጥ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግጥሙ በራሱም ታሪክን ስለሚናገር የሃይማኖት ተከታይ ባይሆንም ይዘቱን መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡"

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ትንሳኤን "አድማቂ" ገጣሚያን- ኤፍሬም ስዩም

"ከጀርባህ ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት፣

እኛን የመውደደህ የዘላለም ብስራት፣

የፋሪስ የሳዱቅ ያለማመን ደባ፣

የጲላጦስ ግርፊያ የሄሮድስ ካባ…"

እያለ እየሱስ ክርስቶስ በሰሞነ ህማማት ያየውን ፍዳና እንግልት በቃላቱ ስሎ፣ በድምጹ አጅቦ ለአድማጭ እንካችሁ የለው ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም፣ መልዕክቱ ሁሉም ዐይነት አድማጮች የሚረዱት መሆኑን ፣ሆኖም አድማጮች(ተከታዮች) ግጥሙን ለሚያመልክው ፈጣሪው እንዳቀረበው የግል መባ እንዲያዩለት እንደሚፈልግ ያስረዳል፣

"ብዙ የክርስትና ዕምነት የማይከተሉ ጓደኞች አሉኝ። አብዛኛዎቹ የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው። ሃሳቤን በጣም የሚገርምና የሚያም ነው ይሉኛል። ይህን ህመም ለመረዳት ክርስቲያን መሆን አይጠበቅባቸውም። እኔ ሃሳቡን በተረዳሁበት መንገድ እነሱም ይረዱታል። እንደ አንድ የስነ ጽሁፍ ሰው እኔ ለማምነው ክፍል ሃሳቤን መሰዋእት አድርጌ አቀርባለሁ። ይህ ለፈጣሪዬ ቀረብ መሰዋዕት ነው። አብዛኛዎቹ የሃይማኖቱ ተከታይ ያልሆኑት ሰዎች ግን 'ሃሳቡ በጣም ደስ ይላል!' ይሉኛል። ማንም ላይ ሃሳቤን እየጫንኩኝ ሳይሆን የተሰማኝን እየገለጽኩኝ ነው፤" ሲል ይደመድማል።