በሞያሌ ከተማ በደረሰ ፍንዳታ በህይወት እና በአካል ላይ ጉዳት ደረሰ

ሞያሌ ከተማ

በሞያሌ ከተማ በተፈጠረ ግጭት አራት ሰዎች ሲገደሉ ቁጥራቸው ከ60 በላይ የሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ በሞያሌ ከተማ መናሃሪያ አካባቢ በኦሮሞ እና በሶማሌ ተወላጆች መካከል ግጭት ከተከሰ በኋላ የእጅ ቦንብ ተወርውሮ ቢያንስ ሁለት ግለሰቦች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል።

የሞያሌ ወረዳ ጤና ጣቢያ ጽ/ቤት ምክት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሁሩካ ጎዳና ለቢቢሲ እንደተናገሩት በፍንዳታው ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና ወደ 63 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከዞኑ የኮምዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለተው የሟቾቹ ቁጥር አራት የደረሰ ሲሆን እድሜያቸው በሃያዎቹ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። ከድሮ ገለቶ፣ ሚፍታህ አብዱራህማን፣ ጀማል አህመድ እና አንደኛው ስሙ ያልታወቀ በክስተቱ ህይወታቸው መጥፋቱ ተረጋግጧል።

በጠዋት ተነስተው ለገበያ የወጡ ሰላማዊ ሰዎች መካከል ቦምቡ እንደፈነዳ የሚናገሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ወዲያውኑ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንና ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልፀዋል። ''አሁን ያለነው ሆስፒታል ውስጥ ነው። ብዙ የተጎዳ ሰው እያየሁ ነው። ይህንን ያደረሱበን የልዩ ሀይል ፖሊሶች ናቸው።''

የአይን እማኙና የቦረና ዞን ኮምዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ገልማ ቦሩ ለክስተቱ መነሻ የሆነው ነገር፤ በአካባቢው ያለ ፍርድ ቤት አጥር ግንባታ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ቀደም ሲል ጀምሮ የፍርድ ቤቱ አጥር ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንዲሁም ከዚህ በፊትም አጥሩ እንዳይሰራ ሲከላከሉ ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል ግጭቱ የጀመረው በኦሮሚያ ፖሊስ በተዘጋጀ ኃይል ነው የሚሉት ደግሞ ሌላ የአይን ምስክር ናቸው። ''ድንጋይ ውርወራን የመሰለ ረብሻ በሚያደርጉበት ጊዜ ከኦሮሚያ ፖሊስ መሃል አንዱ ቦንብ ከእጁ አምልጦ በመፈንዳቱ የ4ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፤ በበርካቶች ላይም አደጋ ደርሷል'' ብለዋል።

ለግጭቱ መነሻም ትናንት የኦሮሚያ መስተዳድር ቢሮዎች የማስፋፊያ ሥራ ለመስራት በሚፈልግበት ጊዜ እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።

ግንባታውን አታካሂዱም በሚል ብጥብጥ ለማንሳት እንደተሞከረ የሚናገሩት አቶ ገልማ ቦሩ ''ትላንትና ይህንን ችግር ለማርገብ ውይይት ተካሂዶ ነበር። ከትላንት ጀምሮ ከሶማሌዎች በኩል ድንጋይ ውርወራ ነበረ። የአካባቢው ወጣቶችም መልሰው መወርወር ጀመሩ። በዚህም ሰዎች ተጎድተዋል። ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ድንጋይ መወራወሩ ቀጥሎ። ህዝቡ ድንጋዩን ለመሸሽ ሲሞክር ቦንብ ተወረወረ'' በማለት ስለክስተቱ ይናገራሉ።

ከሳምንታት በፊት በሞያሌ ከተማ በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በስህተት ተፈጸመ በተባለ ግድያ 10 ሰዎች ተገድለው በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ለደህንነታችን ያሰጋናል በማለት ድንበር ጥለው መሸሻቸው ይታወሳል።