የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፔዎ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሚስጥራዊ ጉዞ አድርገው እነደነበረ ተነገረ

የፖምፔዎ (ግራ) ተልዕኮ የነበረው ትራምፕ እና ኪም ለሚያደርጉት ውይይት ቅድመ ዝግጅቶችን ለማድረግ ነበር Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የፖምፔዎ (ግራ) ተልዕኮ የነበረው ትራምፕ እና ኪም ለሚያደርጉት ውይይት ቅድመ ዝግጅቶችን ለማድረግ ነበር

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት የሲ አይ ኤ አለቃ ማይክ ፖምፔዎ ከሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ጋር ለመወያየት ወደ ፒዮንግያንግ ሚስጥራዊ ጉብኝት አድርገዋል።

የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ወደ ሰሜን ኮሪያ ጉዞ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኪም ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የነበረ ሲሆን ጉዟቸውን ያደረጉት ከአንድ ወር በፊት እንደነበር ስማቸው ያልተጠቀሰ ኃላፊ ተናግረዋል።

ፖምፔዎ ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት ፕሬዝድንት ትራምፕ የውጪ ጉዳይ ኃላፊ አድረገው ካጯቸው በኋላ ነበር።

በፖምፔዎ የሰሜን ኮሪያ ጉብኝት ዙሪያ ዋይት ሃውስ ምንም ያለው ነገር የለም።

ጉብኝቱ ፖምፔዎን እ.አ.አ ከ 2000 በኋላ ከሰሜን ኮሪያ መሪ ጋር የተወያዩ ከፍተኛው የአሜሪካ ባለሥልጣን ያደርጋቸዋል።

እ.አ.አ በ 2004 የቀድሞ የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ በሰሜን ኮሪያ ታስረው የነበሩ ሁለት የአሜሪካ ዜጎችን ለማስለቀቅ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ግን አልተገናኙም።

ፕሬዝዳነት ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ቀጥተኛ ውይይት ስለማድረግ ጠቁመው ነበር።

በፈሎሪዳ የጃፓኑን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤን በማነጋገር ላይ የሚገኙት ትራምፕ ''ከሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የቀጥታ ውይይት አድርገናል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶናልድ ትረምፕ ከኪም ጋር ከስድስት ሳምንታት በኋላ አልያም ከዚያ በፊት ሊገናኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ሁለቱ መሪዎች የት ሊገናኙ እንደሚችሉ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም በርካቶች ደቡብ ኮሪያ፣ ቤጂንግ፣ በእሲያ በአንዱ ሃገር ወይም በአውሮፓ ሊገናኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናትም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያለውን ውጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሞ ጂ-ኢን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ከ 10 ቀናት በኋላ ፊት ለፊት ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ