ዳይመንድ ድረገጹ ላይ በለቀቀውን ቪዲዮ ለእስር ተዳረገ

ዳይምንድ

ከአፍሪካ እውቅ ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው ዳይመንድ ፕላትነምዝ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ከአንዲት ሴት ጋር ሲሳሳም የሚያሳይ ምስል ከለቀቀ በኋላ በታንዛኒያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ፖሊስ የእውቁ ድምጻዊ ተግባር አሳፋሪ እና የማህብረሰቡን እሴት የጣሰ ነው ብሏል።

ዳይመንድ ከሳምንታት በፊት የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኘበት ''ቦንጎ ፍላቭ'' የተሰኘው የሙዚቃ ቪዶዮ በታንዛንያ መንግሥት ወሲብ ቀስቃሽ ምስሎች እና ግጥሞች አሉበት በሚል በአገሪቱ እንዳይታይ ካገደ በኋላ የትውልድ ሃገሩን ጥሎ እንደሚወጣ ዝቶ ነበር።

የኢንፎርሜሽን ሚንስትሩ ሃሪሰን ማክዌምቤ ለምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት ሙዚቀኛው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተላለፈውን የኤሌክትሮኒክ እና ፖስታል ህግጋትን ተላልፏል።

ዳይመንድ በኢንስታግራም ገጹ ላይ የለጠፈውን ተንቀሳቃሽ ምስል የሰረዘ ቢሆንም የታንዛኒያ ባለስልጣናት ግን በሙዚቀኛው ላይ ክስ ለመመስረት ተዘጋጅተዋል።

አምስት ነጥቦች ስለ ዳይመንድ ፕላትነምዝ

  • በምስራቅ አፍሪካ ከባለ ብዙ ጸጋ ሙዚቀኞች መካከል አንዱ ነው
  • ዝነኛ ከመሆኑ በፊት የሰልባጅ ልብሶች ነጋዴ ነበር
  • በቅርቡ የግሉን የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያ ከፍቷል
  • ''ቦንግ ፈላቭ'' የተሰኘ የተሰኘ የታንዛኒያ ሂፕ ሃፕ ዝነኛ አድረጓል
  • በኢንስታግራም ገጹ ላይ 7 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት

ዳይመንድ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የ5 ሚሊየን የታንዛኒያ ሽልንግ ቀጣት ወይም የ12 ወራት እስር ይጠብቀዋል። እራሱን መከላከል ካልቻለ ደግሞ የእስር እና የገንዘብ ቅጣቱ ይጠብቀዋል ተብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የዳይምንድ አድናቂዎች መንግሥት አዲስ ህግ በማርቀቅ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እየተላለፈ ነው በማለት ይተቻሉ።

የታንዛንያ መንግሥት በበኩሉ የአገሪቱን ''ባህል እና ወግ'' እየጠበቅን ነው ይላል።