ከ'ሶፍትዌር' ቀማሪነት ወደ ሥነ-ጥበብ ባለሟልነት

Image copyright MILENA GASHAW
አጭር የምስል መግለጫ ሚሌና ጋሻው

ሚሌና ጋሻው ትውልድ እና እድገቷ በኢትዯጵያ ቢሆንም ከረጅም ዓመታት በፊት ነበር ወደ አሜሪካ ያቀናችው። ሚሌና ነዋሪነቷ በቨረጂንያ ግዛት ሲሆን በአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ቦርድ የሶፍትዌር ፕሮጄክት ኃላፊ ሆና እያገለገለች ነው።

ሚሌና አሁን ያለችበት ቦታ ለመድረስ በትምህርት እና በሥራ ላይ ባሳለፈችባቸው ዘመናት ብቸኛዋ አፍሪካዊት እና ኢትዮጵያዊት ጥቁር ሴት ሆና ዘልቃለች።

ሚሌና ጋሻው ከኮምፒዩተር ክህሎቷ በተጨማሪ በትርፍ ጊዜዋ የተለያዩ የሥነ-ሥዕል ሙያዎችንና የፈጠራ ሥራዎች እንደምትሠራም ነግራናለች። ሚሌና ያለፈችበትን የሕይወት መንገድ እና ስለ ሥራዎቿ እንዲህ አካፈላናለች።

ወላጅ አባቷ አቶ ጋሻው የኪነ-ሕንፃ ባለሙያ የነበሩ ሲሆን ሚሌና ሁሌም በአባቷ የሥዕል ችሎታ በጣም ትመሰጥ ስለነበር መሳል እንዲያስተምራት ትለምነው እንደነበር ነግራናለች።

ለጥበብ ልዩ ፍቅር ስለነበራት የአባቷን የሥዕል ሥራዎች አስመስሎ ለመሳል በምታደርገው ጥረት የምታገኘው ውጤት የተለየ ስለነበር ተስፋ ቆርጣ ትታው እንደነበር ትናገራለች።

ከ 30 ዓመታት በኋላ ግን ለሥነ-ሥዕል ያላት ፍቅር በውስጧ እንደቀረ የተሰማት ሚሌና በዩትዩብ ቪዲዮዎች እየታገዘች እራሷን ማስተማር እንደ ጀመረች ትናገራለች።

Image copyright MILENA GASHAW
አጭር የምስል መግለጫ የሚሌና ፈጠራ ሥራ

ለኮምፒዩተር እውቀቷ የአባቷ ድረሻ ከፍተኛ እንደሆነ የምታስታውሰው ሚሌና የሚያስደስታትን ነገር እንድትሠራ አባቷ ያበረታቷት እንደነበረ እና ሥራ በፆታ እንደማይገደብ እንዳስተማሯት ትናገራለች።

''አባቴ ጎማ መቀየር ፣ ቤት ቀለም መቀባት፣ መፈታታትና መገጣጠም ያስተምረኝ ነበርና የወንድ ሥራ ስለሆነ ወንድ ልጅ ውለድ ስለው ይቆጣኝ ነበር'' ትላለች።

ኮምፕዩተር በሰፊው በኢትዮጵያ ውስጥ በማይገኝበት ዘመን በአባቷ ኮምፕዩተር ትጫወት የነበረችው ሚሌና ወደ አሜሪካ ለትምህርት በሄደችበት ጊዜም ከኮምፕዩተር ትምህርት ውጪ የሚያስደስታትን ልታገኝ ባለመቻሏ ወደ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ ገብታ በጊዜ ሂደት የሶፍትዌር ዲቬሎፕመንት ባለሙያ እንደሆነች ትናገራለች።

''መጀመሪያ ላይ በጣም ከባድ ነበረ። ትምህርቱ ሳይሆን የሚከብደው ብቸኝነቱ ነበር። ብቸኛዋ ሴት፣ ብቸናዋ ጥቁር፣ ብቸኛዋ አፍሪካዊትና ብቸኛዋ የሌላ ሃገር ዜጋ ስለነበርኩኝ በአከባቢዬ ያሉት ሰዎች ስለምንም ጉዳይ የማውቅ አይመስላቸውም ነበር'' ትላለች።

በእራስ መተማመኗ ግን ነገሮች እንዲበግሯት ያልፈቀደችው ሚሌና፤ በትምህረቷ ገፍታ መመረቅ ችላለች። ''የፈጠራ ሥራ ስለምወድ የሶፍትዌር ዲቬሎፕመንትን በጣም ወደድኩት። ሳይንስም ሆነ ቴክኖሎጂ ቢሆንም የፈጠራ ጎን ስላለው መጨረስ አላቃተኝም ነበር'' ብላለች።

ከተመረቀች በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን የሠራችው ሚሌና ከ 5 ዓመታት ወዲህ በአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ውስጥ የሶፍትዌር ዲቬሎፕመንት ፕሮጄክት ኃላፊ ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

ሚሌና አሁንም ብቸኛዋ ጥቁር አፍሪካዊትና ኢትዮጵያዊት ሴት በመሆኗ ደስታና ኩራት እንደሚሰማት ትናገራለች።

Image copyright MILENA GASHAW
አጭር የምስል መግለጫ የሚሌና ልጅ በተራዋ ሌሎች ልጆችን ስታስጠና

ልጆቿ ጠንካሮች እንደሆኑ የምትናገረው ሚሌና ሁለት ሴት ልጆቿን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሰማሩ ከማበረታት ወደኋላ እንደማትል ነግራናለች። ሴቶች ብዙ ስለሌሉ ሴት ልጆችን እንዲወዱት ማድረግ፣ እንደሚችሉ ማሳወቅና ማበረታታት አስፈላጊ ነው ትላለች።

ልጆቿም 'ልጆች ለልጆች' (ኪድስ ቱ ኪድስ) የሚል ፕሮግራም በማዘጋጀት በየተወሰነ ጊዜ እየተሰባሰቡ የቡድኑ አባላት በየተራ ተሽለው በሚገኙበት የትምህርት ዘርፎች ለሌሎች ድጋፍ ይሰጣሉ።

ከሁሉም በላይ መረዳዳትና መረጃ መለዋወጥ ለማህበረሰቡም ቢሆን እድገት የሚያስገኝ መሆኑን የገለፀችው ሚሌና ''እርስ በእርሳችን ብንረዳዳ ጥሩ ነው'' ትላለች።

ሚሌና ወደ ሥዕል የተመለሰችው ከ 30 ዓመት በኋላ ቢሆንም አሁን ያለችበትን ለማመን እንደሚከብዳት ትናገራለች።

ከዚህ በፊት በወረቀት ላይ ብቻ የሥዕል ሥራዎችን ትሠራ የነበረቸው ሚሌና ከዚህ ቀደም አድረጋው ባማታውቀው መልኩ አንድ ቀዳሜ ምሽትን በሙሉ በሥዕል ሸራ (ካንቫስ) ላይ ስትሠራ ማምሸቷን ታስታውሳለች።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሸራ ላይ የሠራችውን ሥዕል በማህበራዊ ገጿ ላይ ለቀቀችው። በማግስቱ በሥራዋ ላይ የተሰጧት አስተያየቶች በጣም የሚያስደስቱና የሚያበረታቱ ከመሆናቸውም በላይ ሥዕሏን አይቶ የወደደላት አንድ ግለሰብ ሊገዛት እንደሚፈልግ አሳውቋት ገንዘቡን እንዳስተላለፈላት ትናገራልች።

''ደነገጥኩኝ! ወደፊት ምናልባት ከ 5 ዓመታት በኋላ እንጂ አሁኑኑ እሸጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር'' የምትለው ሚሌና እሰካሁን የሠራቻቸው ሥዕሎች በሙሉ እንደተሸጡላት ትናገራለች።

Image copyright MILENA GASHAW
አጭር የምስል መግለጫ የሚሌና ጋሻው የሥዕል ሥራዎች በአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ለሕዝብ እይታ ቀርበዋል

በመሥሪያ ቤቷ የሚዘጋጀው የሥዕል ውድድር ላይ 3 ሥዕሎቿን አቅርባ ሁለቱ እንደተመረጡላት የምትናገረው ሚሌና በውድድሩ የተሳተፉት ሰዎች ከሚሌና በልምድ የሚልቁ እንደነበሩ ትናገራለች።

የተመረጡት ሥራዎቿ በፌደራሉ ሪዘርቭ ለ 6 ወራት ለሕዝብ እይታ ቀርቦ በፈረንጆች በዚህ ወር መጨረሻ እንደሚወርድ ትናገራለች።

ሚሌና የፈጠራ ፍላጎቷንና ችሎታዋን ከሶፍትዌር ወደ ሥዕል ሸራ ብታመጣውም በዚህ ብቻ አይገደብም ትላለች።

የፎቶግራፍ ሥራዎች፣ ሴራሚክና ግራፊክስ ዲዛይን የመሳሰሉትንም እንደምትሠራ ትናገራለች። ጀርኒ ቱ ላሰታ የተሰኘውንና ባለቤቷ ፕሮድዩስ ላደረገው ፊልም የሚያስፈልጉትን የማስተዋወቂያ ሥራዎች ከዛሬ 12 ዓመት በፊት ሠርታለች።

ወደፊት ደግሞ እነዚህን የተለያዩ ሥራዎች በአንድ ላይ ለእይታ የማቅረብ ዕቅድ እንዳላትና እራሷን ሳታስጨንቅ ቀስ እያለች ቢያንስ ወደ 60 ሥራዎችን ለማቅረብ እየሠራች ትገኛለች።

Image copyright MILENA GASHAW
አጭር የምስል መግለጫ የሚሌና ጋሻው የፈጠራ ሥፍራ

አበባዎቸን በመጠቀም የማስዋብ ሥራዎች ትሠራ የነበረችው ሚሌና በዚህ ሥራ ትርፍ ማግኘት ባለመቻሏ ሥራውን ለማቆም እንደተገደደች የምታስታውሰው ሚሌና መኖሪያ ቤቷን ለማስጌጥ ግን ምርጫዋ አበባ እንደሆነ ትናገራለች።

ኤች ጂ ቲቪ በተሰኘ የቴሌቪዥን ጣቢያ 'ዲዛይነ ቱ ሴል' ፕሮግራም ላይ የአንድን ሰው ቤት በሳምንት ውስጥ አሳምሮና አስውቦ በማቅረብ ከዋና ዲዛይሯ ጋር ትሠራ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የሪል እስቴት ቤቶችን ለሽያጭ ከማቅረባቸው በፊት የማሳያ ቤቶችን የማስጌጥ ሥራ ሠርታለች።

''ይህንን ሁሉ ሥራ መሥራት ያዝ ለቀቅ እንደ ማድረግ ሆኖ ይሰማኝ ነበር'' የምትለው ሚሌና በእነዚህ የተለያዩ ዘርፎች በመሰማራቷ አሁን ለምትሠራቸው የፈጠራ ሥራዎችና ላቀደችው ዓውደ-ርዕይ መስመር እየያዙላት እንደሆነ ትናገራለች።

''ብዙ ጊዜ የምንወደውን ነገር ከመሥራት የሚገድበን ፍርሃት ነው'' ሰው የሚወደውን ነገር በድፍረት መሞከር አለበት ምክንያቱም ደስታ የሚያስገኝ የሚወዱትን መሥራት ነው'' ትላለች።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሚሌና ጋሻው ነዋሪነቷ በአሜሪካን ሃገር ቨረጂንያ ግዛት ሲሆን ለአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ቦርድ የሶፍትዌር ፕሮጄክት ኃላፊ ሆና ነው ታገለግላለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ