የሹመቶቹ ፖለቲካዊ አንድምታ

Image copyright OPDO

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትናንት የተለያዩ ሹም ሽረቶችን አካሂዷል።

ከሹም ሸረቶቹ መካከል የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረው የፌዴራል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚንስትር የነበሩት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው መሾማቸው እና የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው መሾመቸው ነው።

ከክልሉ የተሰጠው መረጃ እንደሚያሳየው ይህ ሹመት የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍና አዲስ ለውጥ ለማምጣት ታስቦ የተደረገ ነው። በዚህ ሹመት አዳዲስ ግለሰቦች እና ሴቶችም ብቅ ብለዋል።

የተቃዋሚው ጥምር ፓርቲ መድረክ ከፍተኛ አመራር የሆኑት እና ለረዥም ዓመታት የምክር ቤት አባል የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሹም ሽረቱን ፖለቲካዊ አንድምታ ሲገልጹ ''በአጠቃላይ በሃገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሕዝቡ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ ተስፋ ሰንቋል። ነገር ግን የሹም ሸረቱን ፖለቲካዊ አንድምታ ስንመለከት ብዙ ተስፋ ሰጪ አይደለም'' ይላሉ።

ፕሮፌሰር በየነ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ''ታማኝ የሆኑ የፓርቲ አባላትን ነው ቦታ የሚቀያይሩት እንጂ አዲስ ነገር እየፈጠሩ አይደለም። አዲስ የተሾሙት ግለሰቦች የኢህአዴግ ፖሊሲዎችን እስካሰፈጸሙ ድረስ ከአንድ ሥልጣን ወደ ሌላ መሸጋገራቸው ብዙ ለውጥ አያመጣም'' ሲሉ ይሞግታሉ።

ሌላኛው በሃገራችን የፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚታወቁት እና የቀድሞ የፖርላማ አባል የነበሩትን አቶ ገብሩ ገብረማርያምን ሹመቱን በተመለከተ ''አቶ ለማ መገርሳ በክልላቸው ውስጥ ትግላቸውን ያለምንም ተጽዕኖ እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል። ይህንንም በተግባር እንዲያሳዩን እንጠብቃለን'' ይላሉ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዳዲስ ሹመቶችን ከሰጣቸው መካከል ወጣት ፖለቲከኞችን እና ሴቶች ይገኙበታል። ወጣቶችን እና ሴቶችን ወደ ፊት ማምጣቱ የሚኖረው ትርጉም ምንድነው ለሚለው ጥያቄ አቶ ገብሩ ሲመልሱ፤ ''በሃገራችን እየተካሄደ ካለው ለውጥ ጋር መራመድ ከቻሉ እና ሕዝቡ ለሚያነሳው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የሚችሉ ከሆነ መልካም ለውጥ ማየት እንችል ይሆናል። ነገር ግን ከዚህ በፊት የተለመደውን ነገር ይዘው የሚመጡ ከሆነ ግን ለክልሉ አመራር የሚሰጡት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለም'' ይላሉ።

ፕሮፌሰር በየነ በበኩላቸው ''ወጣት እና ሴት ፖለቲከኞች ወደ ፊት መጡ ስለተባለ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ይላሉ። ወጣት እና ሴቶችን ወደፊት ማምጣት አይደለም፤ የኢህአዴግ አባላት ሙሉ በሙሉ ቢቀየሩ እንኳ የፓርቲውን ፖሊሲ እስካሰፈፀሙ ድረስ ምንም ለውጥ አይመጣም'' ሲሉ ይሞግታሉ።

ተያያዥ ርዕሶች