ዚምባብዌ በሺህ የሚቆጠሩ ነርሶችን አባረረች

የዚምባብዌ ነርሶች Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የዚምባብዌ ነርሶች ማህበር ውሳኔውን መከታተላቸውንና በአድማው ግን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል

ባለፈው ሰኞ አድማ አድርገው የነበሩትን ከ 10ሺ በላይ የሚሆኑ ነርሶች ዚምባብዌ ከሥራ ገበታቸው አባረረች።

ምክትል ፕሬዚዳንት ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ነርሶቹ ደምወዛቸውን ለመጨመር ታስቦ 17 ሚልዮን ዶላር ከተለቀቀም በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።

ነርሶቹ ''የሰውን ሕይወት ለማዳን'' ወደ ሥራ ገበታቸው ስላልተመለሱ ምክትል ፕሬዝደንቱ ኮንነዋቸዋል።

ወኪሎች እንደሚናገሩት ከሆነ ይህ ነርሶቹን ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ግፊት ማድረጊያ ዘዴ ነው ይላሉ።

ለፕሬዘዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የጤናውን ዘርፍ መሻሻል ፈተና ሆኖባቸዋል። በቅርቡም የዶክተሮችን የሥራ አድማ ለማስቆም ክፍያቸውን ለመጨመር ተስማምተው ነበር።

ቀድሞው የወታደራዊ ኃይል ኃላፊ የነበሩትና ሮበርት ሙጋቤን ከስልጣን ለማውረድ ይታገሉ የነበሩት ጄን ቺዌንጋ በሰጡት መግለጫ ላይ ''መንግሥት አድማ ያደረጉትን ነርሶች ከሥራ ለማባረር የወሰነው የታመሙ ሰዎችን ሕይወት ለማዳን ባለው ፍላጎት ነው'' ብለዋል።

ቀጥለውም ሥራ አጥ የሆኑና ጡረታ የወጡ ነርሶች የተባረሩትን ነርሶች እንዲተኩ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በምላሹም የዚምባብዌ ነርሶች ማህበር የምንግሥትን ውሳኔ እያጤኑት እንደሆነ እና በአድማው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።