ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምክር ቤቱ የቀረቡት የካቢኔ ሹመቶች በሙሉ ድምጽ ጸደቀ

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምክር ቤቱ የቀረቧቸው የካቢኔ አባላት እጩዎች በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። ላለፉት ሰባት ዓመታት በአፈ-ጉባዔነት ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ አባዱላ በመተካት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ በመሆን በሙሉ ድምፅ መመረጣቸውም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ 10 አዳዲስ ሚንስትሮችን በእጩነት ያቀረቡ ሲሆን 6 ሚንስትሮች ደግሞ ከነበሩበት የሚንስትርነት ሥፍራ ወደሌላ እንዲዛወሩ ተደርጓል። ለምክር ቤቱ ቀርበው በሙሉ ድምጽ ሹመት ያገኙ የካቢኔ እጩዎች ስም ዝርዝር ፦

1. አቶ ሽፈራው ሸጉጤ፡ የግብርና እና የእንስሳት ሃብት ሚንስትር፣

2. አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፡ የትራንስፖርት ሚንስትር፣

3. ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም፡ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር፣

4. አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፡ የመንግሥት ልማት ድርጅት ሚንስትር፣

5. አቶ ዑመር ሑሴን: በሚንስትር ማዕረግ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፣

6. ወ/ሮ ኡባ መሐመድ ሑሴን፡ የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር፣

7. ዶ/ር አምባቸው መኮንን፡ የኮንስትራክሸን ሚንስትር፣

8. አቶ ሞቱማ መቃሳ፡ የሃገር መከላከያ ሚንስትር፣

9. ወ/ሮ ፎዚያ አሚን፡ የባህል እና ቱሪዝም ሚንስትር፣

10. አቶ አህመድ ሽዴ መሐመድ፡ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚንስትር፣

11. አቶ ጃንጥራር አባይ፡ የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚንስትር፣

12. አቶ መለሰ አለሙ፡ የማዕድን እና ኢነርጂ ሚንስትር፣

13. አቶ ብራሃኑ ፀጋዬ፡ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣

14. ወ/ሮ ያለም ፀጋዬ፡ የሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚንስትር፣

15. መላኩ አለበል፡ የንግድ ሚንስትር፣

16. ዶ/ር አሚር አማን፡ የጤና ጥበቃ ሚንስትር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እጩዎቹን ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ ከምክር ቤቱ አባላት ሹመቶቹን በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። ከጥያቄዎቹም መካከል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ሦስት ሚኒስትር የመሾም ይገኝበታል።

ከዚህ በተጨማሪም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 2 መለማመጃ ሆነ፤ ሚኒስትሮች በፍጥነት እየተቀያየሩ ነው፤ አደረጃችት ታክቲክ ነው ግን ውጤትን መሠረት አድርጎ መመዘን ይኖርበታል የሚሉ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን፤ ወ/ሮ ሙሉ ገ/እግዚአብሔር ''በአንዳንድ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች እንደገና ዳዴ ልንል ነው ማለት ነው'' ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩም ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሲሰጡ ''የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ 2 የሁለት ዓመት ተኩል ሪፖርት እየገመገምን ነው፤ በግምገማው መሠረት እነዚህ ተሿሚዎች በቀሪው ጊዜ ዕቅዱን እንዲያሳኩ ነው የታሰበው፤ የተሾሙት ኃላፊዎች ከተሾሙበት ዘርፍ ውጭ ጠንካራ የአመራር ብቃትም አላቸው ተብሎ ይታመናል'' ብለዋል።

ሌላው በምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚንስትሩ የቀረበው ጥያቄ የሴቶች ቁጥር አንሷል የሚል ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲመልሱ ''የካቢኔ ሹመት የዘገየበት አንዱ ምክንያት ሴቶችን ለመጨመር ሲባል ነው፤ አሁን ያቀረብኩት ለዚህ ምክር ቤት የሚቀርበውን ሹመት ብቻ ሲሆን ከዚህ ውጭ ማለትም በሚኒስትር ማዕረግ የሚሾሙ ሴቶች ይኖራሉ'' ብለዋል።