ጥበብን ሰላም ለማስፈን መጠቀም የሚፈልገው ሙዚቀኛ

ፍሬሰላም ሙሴ Image copyright FRESELAM MUSSE

ኤርትራ ውስጥ ተወልዶ ያደገዉ ወጣት ድምፃዊ ፍሬሰላም ሙሴ የ15 ዓመት ልጅ እያለ ሙዚቃ እንደጀመረ ይናገራል።

"ሙዚቃ ለእኔ ምስጢር ነዉ። ከሰዎች ጋር ማዉራት ስጀምር ብቻ ነዉ ስለ ሙዚቃ ማሰብ የማቆመዉ። በቀላሉ የምተወዉና የምገልጸዉ አይደለም" ይላል።

በተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ሙዚቃ በመጫወት እራሱን ማሳደግ የጀመረዉ ፍሬሰላም ወላጅ አባቱ ይጫወቱበት የነበረውን ክራርና ጊታርን የመሳሰሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እየተጫወተ እንዳደገ ነዉ የሚናገረዉ።

"ቤተሰቤ ሙዚቃ የተማርኩበት ትምህርት ቤቴ ነዉ። ከኤርትራ እንደወጣሁ ከተለያዩ ኢትዮጵያዉያን ሙዚቀኞች ጋር በተለያዩ መድረኮች ላይ ሠርቻለሁ። ዱባይና ኡጋንዳም መሥራት ችያለሁ።"

Image copyright FRESELAM MUSSE

ጥበብ ለሰላም

ሙዚቃ ለድምፃዊ ፍሬሰላም ቋንቋንና ባህልን ከመግለጽና ከማጉላት አንፃርም በአካልና በሥነ-ልቦና የተለያዩ ሕዝቦች አንድ ላይ እንዲዘምሩና እንዲገናኙ የማድረግ ኃይል አለዉ።

"ሙዚቃ በጠባብ ጎሰኝነት ለተጠቁ ሰዎች ፈዉስ ነዉ። በኤርትራ ውስጥ አንድ ወግ ነበር። በመንግሥታት ግጭት ምክንያት የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ከተዘጋ በኋላ፤ ለሙዚቃ እንኳን የምትሆን ትንሽ ቀዳዳ ተዉሉን ይባል ነበር። ይሄ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለዉ። ሙዚቃ ልብ ዉስጥ የሚኖር ትልቅ ሃብት ነዉ።"

ሙዚቃ ሥነ-ልቦናዊ መነቃቃትን በመፍጠር፣ ጭንቀትና ብስጭትን በመቀነስ ረገድና የባህሪ ለዉጥ እንዲመጣ አስተሳሰብን ከመቅረፅ አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለዉ። በመሆኑም እኛ ወጣቶች የሕዝብን አንድነት በማሳደግ መትጋት አለብን ሲል ሃሳቡ ይቋጫል።

ተያያዥ ርዕሶች