የኩባው መሪ ራዉል ካስትሮ ለሚጌል ካናል ስልጣን አስረከቡ

ዲያዝ ሚጌል ካናል Image copyright AFP

ዲያዝ ሚጌል ካናል እንደአውሮፓዊያኑ በ2006 ከወንድማቸው ስልጣን የተረከቡትን ራዉል ከሳስትሮን በመተካት አዲሱ የኩባ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።

በ1959 ከተካሄደው አብዮት ወዲህ የካስትሮ ቤተሰብ ከመንግሥት ስልጣን ሲርቅ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ዲያዝ ካናል ላለፉት አምስት ዓመታት በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን ከኩባው አብዮት በኋላ ቢሆንም የተወለዱት፤ ዲያዝ ካናል የራዉል ካስትሮ ታማኝ አጋር ናቸው። ይህ በመሆኑም ስር ነቀል ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ፕሬዝዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ''ኩባ ውስጥ ካፒታሊዝምን መልሰው ለማምጣት ለሚያስቡ ሰዎች ቦታ የለም'' ብለዋል።

ተቀዳሚ ሥራዬ የሚሆነው በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የምትገኘውን የኩባን አብዮት ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው ሲሉም ተደመጠዋል።

ዲያዝ ካናል ሲያክሉም የኩባ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደማይቀየርና አስፈላጊ ከሆነ ግን በህዝቡ የሚወሰን እንደሆነ ተናግረዋል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ከአጋራቸው ቬኑዙዌላ ኢኮኖሚ መዳከም ጋረ ተያይዞ የተጋረጠባቸውን አደጋ እንዴት መጋፈጥ እንዳለባቸው ማሰብ ያለባቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የካሪቢያን ደሴት ሃገራት ከአሜሪካው መሪ ዶናልድ ትራምፕ ጋረ ምን አይነት ግንኙነት እንደሚኖራቸውም መወሰን ይጠበቅባቸዋል።

Image copyright AFP

ተያያዥ ርዕሶች