ሴናተር ታሚ ደክዎረዝ ህጻን ልጇን ወደ ሥራ በመውሰድ ታሪክ ሰራች

ከኤሊኖይስ የተወከለችው ዲሞክራቲክ ሴናተር ታሚ ደክዎርዝ Image copyright Inpho

የኤሊኖይ ሴናተሯ ታሚ ደክዎርዝ ህጻናት ወደ አሜሪካ ምክር ቤት እንዳይገቡ የሚከለክለው የቆየ ህግ ከተነሳ ከአንድ ቀን በኋላ ጨቅላ ልጇን ወደ አሜሪካ የላይኛው ምክር ቤት አምጥታታለች።

የሃምሳ ዓመቷ ደክዎርዝ፤ ልጇን በእቅፏ እንደያዘች ለናሳ አመራርነት ለሚደረገው የእጩዎች ምርጫ ድምጿን ሰጥታለች።

በእናቷ እቅፍ ውስጥ ሆና ወደ ምክር ቤቱ የመጣችው ሜይሊ ገና በተወለደች በ10ኛ ቀኗ ነው ታሪክ የሰራችው።

ባለፈው ሳምንት እናቷ በምክር ቤቱ ቢሮ ውስጥ ልጅ በመውለድ የመጀመሪያዋ መሆን ችላ ነበር።

በቀናት ልዩነት ታሪክ መስራት የቻሉት እናትና ልጅ በአሜሪካ የወሊድ ፖሊሲ ላይ ክርክር አስነስተዋል። አሜሪካ ለወሊድ እረፍት ክፍያ የማትፈጽም ብቸኛዋ ያደገች ሃገር ናት።

ባለፈው ረቡዕ የአሜሪካ ሴናተሮች ለቤተሰብ ምቹ የሆነ ፖሊሲ ለሃገሪቱ ምሳሌ መሆን አለበት በማለት ተከራከክረው፤ ህጻናት ወደ ምክር ቤቱ እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ አጽድቀው ነበር።

ሴናተር ታሚ ደክዎረዝ ''ልጄ የምክር ቤቱን የአለባበስ ህግ እንዳትጥስ'' ጃኬት አልብሻታለው ስትል ቀልድ አዘል አስተያየቷን ገልጻለች።

ሴናተሯ በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ እያገለገሉ ልጅ ከወለዱ 10 ሴቶች መካከልም ነች።

ሜይሊ ሁለተኛ ልጇ ስትሆን፤ የመጀመሪያ ልጇ አቢጌልን በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት እያገለገለች ነበር የወለደቻት።

ተያያዥ ርዕሶች