ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የወልቃይት ንግግራቸውን አስመልክቶ ምላሽ ሰጡ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ Image copyright ZACHARIAS ABUBEKER

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ረፋድ ላይ በፋሲለደስ ስታዲየም ባሰሙት ንግግር ጎንደር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታና እና የስኬት እና የጀግንነት ታሪኮች ካነሳሱ በኃላ አሁንም ህዝቡ "በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት'' ከጎናቸው እንዲቆም ጠይቀዋል።

"የስልጣኔ መሰረት፣ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ጌጥና የኩሩ ህዝብ ምድር'' የሚሉ ሙገሳዎችን ያሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሳካት የክልሉና የፌደራል መንግስት እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ ከሰዓት በኋላ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በጎሃ ሆቴል በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የወልቃይት ማንነት ጉዳይ እና ''መሬት ለሱዳን ያለ አግባብ ተሰጥቷል'' በሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ስለነበረው ጉዳይ እንዲሁም ሌሎች በህዝቡ ዘንድ ቅሬታን የፈጠሩ ጉዳዮች እንደተጠየቁ በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወልቃይትን አስመልክቶ ምላሽ ሰጡ

በተለይ የወልቃይት ጉዳይ በተመለከተ በመቀሌ ጉብኝታቸው ላይ ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት መልስ 'የወልቃይትን ጉዳይ ከማንነት ጋር ሳይሆን ከመሰረተ ልማት ጥያቄ ጋር አዳብለውታል፤" ጥያቄውን አቅልለዋል በሚል ከሰሞኑ ቅሬታ ሲሰማ እንደነበረ ይታወሳል።

ይሄንን በመለከተ ከወልቃይት ማንነት መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አታላይ ዛፌን ጨምሮ ከሌሎችም ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቀሌው ቆይታቸው የሰጡት መልስ ወልቃይትን በሚመለከት ለቀረበ ጥያቄ የተሰጠ መልስ ሳይሆን መሰረተ ልማትን በተመለከተ ለተጠየቀ ሌላ ጥያቄ የተሰጠ መልስ መሆኑን ለማብራራት እንደሞከሩ በስብሰባው ላይ የተገኙ ነዋሪዎች በተጨማሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከሁለት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ የጎንደር በከፍተኛነቱ ይታወሳል።