"በሞያሌ ከተማ በነፃነት መንቀሳቀስ ከባድ ሆኗል" የቦረና ዞን ኮሙኒከኬሽን ከሃላፊ

በሞያሌ ከተማ በየጊዜው እየተፈጠረ ባለው ግጭት ምክንያት ነዋሪዎች በነፃነት መውጣት እና መግባት አለመቻላቸውን የቦረና ዞን ኮሙኒኬሽን ሃለፊ አቶ ገልማ ቦሩ ለቢቢሲ ገለፁ።

ሃላፊው እንደሚሉት "በሞያሌ ከተማ በነፃነት መንቀሳቀስ ከባድ ሆኗል።"

ከቀናት በፊት በሞያሌ ከተማ በደረሰው የቦንብ ጥቃት የሟቾች ቁጥር ስድስት መድሰሩን እና አሁንም በከተማዋ ውጥረትና አለመረጋጋት እንዳለ አቶ ገልማ ይናገራሉ።

"በአካባቢው በተደጋጋሚ የማይታወቅ ሰው የጦር መሳሪያ ጥቃት እያደረሰ ነው። በዚህም ምክንያት ሰዎች የለት ተለት ስራቸውን ማከናወን አልቻሉም። የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘዋል። በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ስጋት አለ'' ሲሉም ተደምጠዋል።

ከሳምንት በፊት በከተማዋ በተፈጸመ የቦንብ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን እና ከ60 በላይ የሚሆኑ ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ዘግበን ነበር።

በሞያሌ ከተማ በደረሰ ፍንዳታ የሰው ህይወት ጠፋ

በወቅቱ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ በሞያሌ ከተማ መናሃሪያ አካባቢ በኦሮሞ እና በሶማሌ ተወላጆች መካከል ግጭት ከተከሰ በኋላ የእጅ ቦንብ ተወርውሮ ነበር ጉዳቱ የደረሰው።

የአይን እማኞች ለክስተቱ መነሻ የሆነው ነገር፤ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ ያለ ፍርድ ቤት አጥር ግንባታ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።

የቦረና ዞን ኮሙኒኬሽን ሃለፊ አቶ ገልማ ቦሩ፤ በከተማዋ የተከሰተውን ጥቃት ማን እንደፈጸመ ሲጠየቁ፤ ''እስካሁን አራት ሰዎች የጦር መሳሪያ እንደታጠቁ ተይዘዋል። የእነዚህን ሰዎች ማንነት እና ተልዕኳቸው ምን እንደሆነ እየተጣራ ነው። የምርመራው ውጤት ሳይደርስ ጥቃቱን የፈጸመው እከሌ ነው ማለት አልችልም'' ብለዋል።