እራስን መፈለግ፣ እራስን መሆን ፣ እራስን ማሸነፍ

ሐይማኖት ሆነልኝ Image copyright HAYMANOT HONELGNE

ጥበብን ለዕለት ጉርስ ማግኛ ሳይሆን እራስን ለመግለጥ ብቻ ትጠቀምበት እንደነበር ትናገራለች ሐይማኖት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት የመረጠችው የቤተሰቦቿን ደስታ ላለማክሸፍ ብላ እንጂ በርግጥም በተማረችበት ሙያ ተቀጥራ መንፈሷንም ኪሷንም በእርካታ መሙላት እንደማትችል ቀድሞ ገብቷት ነበር።

በቅድሚያ ሠዓሊ እንደምሆን አውቅ ነበር የምትለው ሐይማኖት የሥዕል ችሎታ እንደነበራት እና እንደምትስልም ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች። እርሷ ወደ ሥዕሉ ብትሳብም ቤተሰቦቿ ግን ለኪነ-ጥበቡ ያላቸው ግንዛቤ ተሰጥኦዋን በትምህርት እንዳታስደግፈው አድርጓታል። ከዚህም ባለፈ እርሷ የሕግ ትምህርት ቤት ብገባ ብላ ታስብ ስለነበር ያ ሳይሆን ሲቀር የቤተሰቦቿን ደስታ ብቻ ለማሳካት የአስተዳደር ሙያ አጥንታ ተመረቀች።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ እያለች ወዳጆቿ በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ነበሩ። እነርሱ በሚያዘጋጇቸው የተለያዩ አውደ-ጥበቦች ላይ እየተገኘች ተሰጥዖዋን ለማሳየት ትጥር ጀመር። የሥዕል ችሎታዋንም ለማዳበር አጫጭር ኮርሶችን ወስዳለች።

Image copyright HAYMANOT HONELGNE
አጭር የምስል መግለጫ እናትና ልጅ ጎዳና ላይ እየሄዱ ያነሳችው ይህ ፎቶግራፍ መቼም አይረሳትም

የፎቶግራፍ ጥበብ

ሐይማኖት ሠዓሊ የመሆን ፍላጎቷን የመኮትኮትና የማሳደግ ሕልሟ በውስጧ እንዳለ ቢሆንም ፎቶ ግራፍ የማንሳት ጥበብ ዝንባሌዋ ደግሞ እያየለ መጣ። ስለዚህ የተለያዩ ፎቶዎችን በስልኳ እያነሳች ለባልንጀሮቿ ታሳይ ጀመር። ከጓደኞቿ የምታገኘው አድናቆትና ውዳሴ ልቧን ያሸፍተው ጀመር።

ከዚያ በኋላ መደበኛ ካሜራ በመጠቀም ስሥዬ ሆይ ብላ ፎቶ ማንሳቱን ገባችበት። ሐይማኖት ፎቶ ስታነሳ እንደሠርግ እና ልደት ያሉ ከበራዎች ላይ ተገኝታ ማንሳት ምርጫዎቿ እንዳልሆኑ ትናገራለች። ከዛ ይልቅ የጎዳና ላይ ትዕይንቶችን እየተከተሉ እና እየፈለጉ በማንሳት የምትፈልጋቸው ቁምነገሮች ጎልተው በሌሎች ዓይን እንዲታዮላት ትፈልጋለች። ባለፈው ዓመትም ያነሳቻቸውን ፎቶዎች ሰብሰብ አድርጋ ለሕዝብ እይታ እንዳበቃች ታስረዳለች።

እነዚህ ፎቶዎች ስሜቷን ለመግለጥ ብቻ ሳይሆን የዕለት ጉርሷንም ለመሸፈን ረድቷታል።

ሐይማኖት ሥራዎቿን ለማስተዋወቅ የማህበራዊ ድረ-ገፆችን እንደመንገድ እንደምትጠቀምበት ትናገራለች። ካነሳቻቸው ምስሎች ባጠቃላይ የማትረሳው እናትና ልጅ ጎዳና ላይ እየሄዱ ያነሳችውን ነው።

ይህንን ፎቶ ስታስታውስም ፎቶ ማንሳት በሽርፍራፊ ሰከንድ ውስጥ ያሉ ኹነቶችን ቶሎ ለቀም አድርጎ መያዝ ነው። ያ ፎቶም እነዚያን ሽርፍራፊ ሰኮንዶችን ያስቀረሁበት ስለነበር በርካቶች ወደውታል ትላለች።

Image copyright HAYMANOT HONELGNE
አጭር የምስል መግለጫ የተለያዩ የዲዛይን ጥበብ ሥራዎቿ

የዲዛይን ጥበብ

ሐይማኖት በተማረችበት ሙያ ለሁለት ዓመት ያህል በተለያየ ቦታ ተቀጥራ ሠርታለች። የፎቶግራፍ ጥበብን እንደ የሕይወት ጥሪ ተቀብላ የጎዳና ላይ ፎቶዎችን እያነሳች እና ፎቶዎችን እየሸጠች ደግሞ በቋሚ ገቢ ማግኛነት መጠቀም እንደማትችል ተረዳች። ይሄኔ እራሷን በእራሷ ወዳስተማረችው የተለያዩ ነገሮችን የማስዋብ ሙያ ፊቷን አዞረች።

በሁለት ዓመት ውስጥ ሦስት ሥራዎችን ቀያይሬ ነበር የምትለው ሐይማኖት፤ ቋሚ የወር ገቢ የምታገኝበትን ሥራዋን ትታ ወደጥበብ ሥራዎች ፊቷን ስትመልስ ቤተሰቦቿም ሆነ ወዳጆቿ "ሐይማኖት ምን ነክቶሻል" የሚል ተግሳፅ እንደገጠማት ታስረዳለች።

ማንም በተሰጥዖዋ ውስጥ እራሷን እንድትፈልግ እና እራስዋን እንድትሆን እንዳላበረታታት የምትናገረዋ ሐይማኖት ይህ ደግሞ ፈታኝ እንደነበረባት አልሸሸገችም።

የተለያዩ ነገሮችን እየሠራሁ ለእራሴም ሆነ ለባልንጀሮቼ እሰጥ ነበር የምትለው ሐይማኖት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራቻቸውን ጆሮ ጌጦች ይዛ በአካባቢዋ ወደሚገኘው 'ድንቅ የአርት ጋለሪ' አመራች።

''እውነቱን ለመናገር ሥራዎቼ ጥሩ አልነበሩም። አዲስ ነገር ለመሥራት ሙከራ ያደረኩባቸው ነበሩ" የምትለዋ ሐይማኖት በአርት ጋለሪው ያገኘቻቸው ሰዎች ምክር እንደለገሷት አትረሳም።

እነዚያን ምክሮች ወስዳ የእራሷን የእጅ አሻራዎች በማሳረፍ መሥራት ቀጠለች። በኋላም በጥሩ ሁኔታ የሠራቻቸውን ጌጣ ጌጦች እዛው ጋለሪ ውስጥ መሸጥ ጀመረች።

ሐይማኖት ሥራዎቿን ለማስዋብም ሆነ የእራሷን አሻራዎች ለማሳረፍ የምዕራብ አፍሪካዊያንን የተለያዩ ውጤቶች እንደምትጠቀም ትናገራለች። ሁልጊዜም ቢሆን አዲስ ነገር ለመሞከር እና እራሷን ለማስተማር እንደምትተጋም ታስረዳለች።

አነስተኛ ጌጣ ጌጦችን ብቻ ሳይሆን የእራስጌ መብራቶችን፣ የትራስ ጨርቆችን ጥለቶችን በመጠቀም እያስዋበች ለሃገር ውስጥ እና ለውጭ ሃገር ደንበኞቿ ትሸጣለች።

Image copyright HAYMANOT HONELGNE
አጭር የምስል መግለጫ የተለያዩ የእጅ ሥራዎቿ

የእጅ ራ ውጤትና ኢትዯጵያውያን

እኛ ሃገር በእጅ ለሚሠሩ ውጤቶች የሚተመነው ዋጋ እጅግ በጣም ዝቅ ያለ ስለሆነ ብዙ ደንበኞች ለማግኘት ያስቸግራል ትላለች ሐይማኖት። ስለዚህ ሥራዎቿን ለመግዛት ከኢትዮጵያውያን ይልቅ የውጭ ሃገር ዜጎች ይደፍራሉ።

ተቀጥሮ መሥራት በገቢ ደረጃ የምትተማመንበት ነገር እንዲኖር ያደርጋል የምትለዋ ሐይማኖት፤ ቋሚ የወር ገቢን ትቶ የእራስን ተሰጥዖ ተጠቅሞ ገቢ ማግኘት ፈተና እንደሆነም አልሸሸገችም።

በመቀጠልም ሐይማኖት ገበያ ለማግኘትም ሆነ ቋሚ የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታ እንዲኖራት ጥረት እያደረገች እንደሆነ ትናገራለች። ነገር ግን ጥረቷን እንደሥራ ፍሬዋ በመውሰድ እና በምታገኛቸው ትናንሽ ውጤቶች ''ደስተኛ በመሆን ዛሬን እየኖርኩ ነገን ትልቅ አልማለሁ'' ትላለች።

አሁን ከተማዋ ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ለሥራዎቿ ገበያ ለማግኘት እንዳገዛት ታስረዳለች። በተለይ አውደ-ርዕዮች ሲበዙ እና ቀን እና ለሊት ከእንቅልፍ ተፋትታ የምትሠራቸው ሥራዎች የበለጠ እንደሚመስጧት ትናገራለች።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሐይማኖት ሆነልኝ ውልደቷ እድገቷ አዲስ አበባ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች