ቡሃሪ እና ትራምፕ ዲሲ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል

ቡሃሪ እና ትራምፕ በዲሲ ሊገናኙ ነው Image copyright Reuters

የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙማሙዱ ቡሃሪ የአሜሪካው አቻቸውን በዋሽንግተን ዲሲ በማግኘት ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። ቡሃሪ በትራምፕ ዘመን ወደ አሜሪካ የሚያቀኑ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ይሆናሉ።

ሁለቱ መሪዎች በምጣኔ ሃብትና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ጊዜ ትራምፕ የአፍሪካ ሃገራትን በፀያፍ ቃል መጥራታቸውን ተከትሎ የሁለቱ መሪዎች ውይይይት ተጠባቂ ሆኗል፤ ምንም እንኳ ሰውዬው "እኔ እንዲህ ዓይነት ስድ ቃል አልወጣኝም" ብለው ቢከራከሩም።

ቢሆንም የቢቢሲው ማዬኒ ጆንስ እንደሚለው ሁለቱ መሪዎች ጠጠር ባሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው ቀጠሮ የያዙት።

ቡሃሪ ሃገር ቤት ከደህንነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች እያስጨነቋቸው እንደሆነ፤ በተለይ የቦኮ ሃራም ጉዳይ ትንፋሽ እንዳሳጠራቸው ነው ተንታኞች የሚገልፁት።

ሽብርተኝትን መወጋት የሁለቱ መሪዎች ውይይት ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆንም የተጠበቀው ለዚሁ ነው።

አሜሪካ በቅርቡ 12 ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችም 496 ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ዋጋ ለናይጄሪያ መሸጧ የሚታወስ ነው።

በቀጣይ ዓመት በናይጄሪያ በሚደረገው ምርጫ እሳተፋለሁ ብለው መግለጫ የሰጡት ቡሃሪ የዴሞክራሲ ግንባታን ሥር ለማስያዝ እየተጋሉ ቢሆንም ሙስኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሃገሪቱ መስፈኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

ቡሃሪ ከትራምፕ ጋር ያላቸውን ውይይት ሲያጠናቅቁ ከንግድ ሰዎች ጋር ለመወያየትም ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል።

ነባር የሁለቱ ሃገራት ባለሥልጣናት የሚያካሂዱት የሁለትዮሽ ንግግርም የቡሃሪ ጉብኝት አካል ነው።