የሕይወትን ክር ጫፍ ፍለጋ

ዮሴፍ ሰቦቅሳ Image copyright YOSSEF SEBOKSA
አጭር የምስል መግለጫ ዮሴፍ ሰቦቅሳ

በልጅነቱ ቤት ውስጥ የነበሩ አሻንጉሊቶችን ደብተሩ ላይ እያስመሰለ ለመሳል ይሞክር እንደነበር ቤተሰቦቹ ያስታውሳሉ፤ ሰዓሊ ዮሴፍ ሰቦቅሳ። "ስዕልን ከልጅነቴ ጀምሮ ውስጤ እንደነበር ይሰማኛል" የሚለውም ለዚህ ነው።

እርሱ እንደሚለው እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ ስዕልን ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው የትምህርት ዓይነት አልነበረም። እንደማንኛውም የከተማ ልጅ የእንቁጣጣሽ ስዕሎችን እየገዛ ደግሞ እየሳለ በመሸጥ አሳልፏል።

በ13 ዓመቱ ወደ ሰባተኛ ክፍል ሲሸጋገር ግና ስዕል የሕይወት ጥሪው፤ የወደፊት የኑሮ ዘይቤው መሆኑ ይገለጥለት መጣ።

"ያኔ ነው ወደ ሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል በመሄድ የስዕል ትምህርትን መከታተል የሻትኩት" ይላል።

ለጥቆም ወደ አቢሲኒያ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ዘለቀ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ሲያጠናቅቅ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት ተሰጥኦውን በትምህርት ያዳብር ያዘ።

ፍለጋው አያልቅም. . .

ዮሴፍ ስለስዕሎቹ ሲናገር "መጀመሪያዬም መጨረሻዬም ይመስለኛል" ይላል። ሸራ ወጥሮ ሃሳቦቹን በወጉ በብሩሽ ማስፈር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ እንዲሁም ወደፊትም ስራዎቹ አልፋ እና ኦሜጋቸውን ፍለጋ ላይ እንዳደረጉ ሲናገር በምስጠት ነው።

ፍለጋ ላይ ማተኮሩን የተያያዘው በ2006 ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቀጣና ካቀና በኋላ እንደሆነ የሚናገረው ዮሴፍ ወደ ዩኒቨርስቲ ከገባ በኋላ የስዕል ሃሳቦችን ሲያሰላስል ያሳለፋቸውን ሕይቶች መሳል መፈለጉ ትዝ ይለዋል።

በዛ ወቅት በልጅነቱ ይወደው የነበረው ትኩስ እንጀራ አእምሮው ውስት የትዝታ ማህደሩን ዘረጋ።

"ትኩስ እንጀራ ብቻ ሳይሆን ድርቆሽም ከምወደው መካከል ነው" ይላል ዮሴፍ፤ ያንን ሲያስታውስ ደግሞ እንጀራውም ሆነ ማሰሻው ተነጣጥለው አልታዩትም፤ ማሰሻ እና ምጣድ መልኩ ያማረ እንጀራ ለማውጣት ያላቸውን ዝምድና በማሰብ ወደ እይታዊ ጥበብ የመቀየር ሃሳብ አእምሮውን ወጥሮ ያዘው።

Image copyright YOSSEF SEBOKSA
አጭር የምስል መግለጫ ማሰሻ

በዩኒቨርስቲ ቆይታው ስራዎችን እንዲሰራ ሲታዘዝ ማሰሻን በመውሰድ ማሰስ የሚል ነገር በማፍለቅ ትኩረቱን አደረገ።

ማሰስ መፈለግ የሚለውን የህይወት ትርጉም ከዚህ በመውሰድ ምንድን ነው የምናስሰው? ምንስ ነው የምንፈልገው? የሚለውን በስእል ስራዎቹ ውስጥ ለማሳየት እንደሚጥር ይናገራል።

የማሰሻ እና የምጣድ መገናኘት ጥሩ እንጀራ ለማግኘት ዋስትና መሆኑን በማየት ምጣድን የዓለም ተምሳሌት አድርጎ በመውሰድ በርካታ ስራዎችንም ሰርቷል።

''የሰው ልጅ በዚህች ክብ ዓለም ሲኖር የተለያዩ ነገሮችን ለማሳካት፣ ሕልሙን እውን አድርጎ ለመጋገር እና ቆርሶ ለመብላት የተለያዩ ነገሮችን ያስሳል" የሚለው ዮሴፍ ይህ ሃሳብ ከትናንቱ ጀምሮ የስዕል ስራው ማጠንጠኛ ተምሳሌት በመሆን እያገለገለው እንደሆነ አበክሮ ይናገራል።

በመቀጠልም የተለያዩ ጤፍ እንጀራ አይነቶችን በመጠቀም፣ ማሰሻውንና፣ እንደማሰሻ የምንገለገልበት የጎመን ዘርን በምሳሌነት በመጠቀም ስራዎቹን እንደሚሰራ ያስረዳል።

እኛና ቴክኖሎጂ

ዛሬ ፍለጋውን ከዚህ ባሻገርም እንዳሻገረ የሚያስረዳው ዮሴፍ ያለንበትን የመረጃ ዘመን የፍለጋው አካል እንደሆነ ለማሳየት የተጠቀመበትን እና ስራዎቹን ለህዝብ ያቀረበበትን አውደ ርዕይ በምሳሌነት ያነሳል።

በ2008 ድንቅ አርት የስነ-ጥበብ ውጤቶች ማሳያ 'ሪፍሌክሽን ቁጥር 2' ላይ ያቀረበውና የሰው ልጅ በድረ-ገፆች ውስጥ በፍለጋ እንዴት እንደተወሰደና እንደሚማስን ለማሳየት የተለያዩ የኮምፒውተር ቁሶችን በመጠቀም ያቀረበውን ስራ ለአብነትም ይጠቅሳል።

የሰው ልጅ እና ቴክኖሎጂ ምን ያህል እንደተሳሰሩ ያሳየበትና የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅም ለመመረቂያ ስራው የሆነውን ስራ በመሆኑም ከየትኛውም ስራው በበለጠ ያስታውሰዋል።

ስራው ይላል ዮሴፍ "ስራው የማዘር ቦርድን በመጠቀም የተሰራ ነው። ማዘር ቦርድ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማንቀሳቀስ የምንጠቀምበት ነው። የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር የደም ዝውውሩን ወዲህ ወዲያ የሚያደርጉ የደም ስሮች እንዳሉት ሁሉ በማዘር ቦርዶቹም ላይ የተለያዩ መስመሮች፣ ቅርፆች፣ መነሻዎች አሉ። እነዚህን ማዘር ቦርድ ላይ ያሉ መስመሮች፣ መነሻዎችና ነጥቦችን እንደ የጥበብ አላባ በመውሰድ ግማሽ የሰው ፊት ግማሽ ማዘር ቦርዱን በማድረግ የሰው ልጅና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ዝምድና ያሳየሁበት አውደ ርዕይ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ስራዬ ነው" ይላል።

Image copyright YOSSEF SEBOKSA
አጭር የምስል መግለጫ ከፊል የአብስትራክት አይነት ስዕሎች

ሰዓሊ ዮሴፍ ከስነጥበብ ትምህርት ቤት ተመርቆ ከወጣ በኋላ 15 ያክል የስዕል አውደ ርዕዮችን ለብቻውም ሆነ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን አቅርቧል።

በአሁኑ ሰአት ከፊል ረቂቅ ወይም 'አብስትራክት' ስዕሎች ላይ እንሚያተኩር የሚናገረው ዮሴፍ አብዛኞቹ ስራዎቹ ግን ተምሳሌታዊ መሆናቸውንም ይገልፃል።

በታህሳስ ወር 'ሪፍሌክሽን ቁጥር 3' ብለው ከሙያ አጋሮቹ ጋር ያሳዩት የስዕል አውደ ርዕይ ድጋፍም ነቀፋም ያገኘበት እና ትልቁ መድረክ እንደሆነ የሚናገረው ዮሴፍ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ ሰዎች መምጣታቸው ፍሰሃ እንዳላበሰው ያስታውሳል፤ "ይህ ትልቁ መድረኬ እና ስኬቴ ነው" በማለትም ይገልፀዋል።

ስዕል እና ገቢ

ሰዓሊ ዮሴፍ ስዕልን ገቢው አድርጎ እንደሚኖር ይናገራል። አሁን በከተማችን ስዕልን እንደገቢ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ለሚፈልጉ ጥሩ ጊዜ እንደሆነም ይመሰክራል። "አሁን በቅርቡ እንኳ የሸጥኩት ስዕል 32000 ብር ያወጣ ነው" ይላል ከገቢ አንፃር ያለውን ትርፍ ሲያስረዳ።

ዮሴፍ ለወደፊት የስዕል ስራዎችን ይዞ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የማሳየት ሕልም አለው፤ "ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ እንኳ ስራዎቼን ለህዝብ ባቀርብ፣ በዓለም ዙሪያ ተዘዋውሬ ስራዎቼን ባሳይና እኔም ሀገሬም ብንጠቀም ስል አልማለሁ።"

ተያያዥ ርዕሶች