ካለሁበት 31፡ ''ብዙ ትውስታዎቼ ከዛፍና ከጭቃ አያልፉም''

አሊዩን ፋይ Image copyright ALIOUNE FAYE

ስሜ አሊዩን ፋይ ይባላል፤ ኢትዮጵያዊው ስሜ ግን ሚኪያስ ነው። እናቴ ኢትዮጵያዊት አባቴ ደግሞ ሴኔጋላዊ ነው። አሁን የምገኘው በአሜሪካዋ የኦርላንዶ ከተማ ቢሆንም ዋና መኖሪያዬ ግን ቫንኩቨር ካናዳ ነው።

በሥራዬ ፀባይ ምክንያት የሚቀጥለው ሳምንት ለምሳሌ ወደቬጋስ አቀናለሁ። ቀጥዬም ሥራዬ ወደሚያስጉዘኝ ሌላ ከተማ። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በየሳምንቱ አልፎ አልፎ ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እየተዘዋወርኩ ነው የምሠራው።

ለሁለት ዓመታት ተቀጥሬ እየሠራሁ ቆየሁ፤ አንድ ቀን ግን ሕይወቴን መቀየር እንዳለብኝ ተሰማኝ። ወጣት ስለሆንኩኝና በሥሬ የሚተዳደር ሰው ስላልነበረኝ በአንድ ቦታ የመቀመጥ ግዴታ እንደሌለብኝና ዓለምን ባያት ጥሩ መስሎ ታየኝ።

ጊዜው የቴክኖሎጂ በመሆኑና እኔ ደግሞ ቴክኖሎጂ በጣም ስለሚያስደንቀኝ በእራሴ ሥራ ለመሰማራት ወሰንኩኝ። ቴክኖሎጂ ዓለማችንን የመቀየር ኃይል እንዳለው አምናለሁ።

አሁን ለተለያዩ ድርጅቶች የተለያዩ ዝግቶችን በወረቀት አልባው የእጅ ስልክ መተግበሪያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከሃገር ሃገር፣ ከከተማ ከተማ እየተዘዋወርኩ በማቅረብ ነው የምተዳደረው።

Image copyright ALIOUNE FAYE
አጭር የምስል መግለጫ ሃዋይ እያለሁ ያነሳሁት የቀስተ ደመና ፎቶግራፍን ይህን ይመስላል ይላል አሊዩን

ከዚህ ሥራዬ በተጨማሪ ደግሞ በትርፍ ጊዜዬ ሙዚቃ ለተለያዩ ዝግጅቶች አቀናብራለሁ፤ ይህንን የማደርገው በኢትዮጵያዊው ስሜ ነው።

ከኢትዮጵያ የወጣሁት በ15 ዓመቴ ነበር። እዚያ እያለሁ የቤት ልጅ ስለነበርኩ ብዙ ትውስታዎቼ ከዛፍና ከጭቃ አያልፉም። እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያ ዛሬ ነገ እመለሳለሁ ስል ሳላስበው ይኸው 14 ዓመታት አስቆጠርኩኝ።

ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ አስባታለሁ፤ ብዙ ጊዜ በሃሳብ ጭልጥ ብዬ እንድነጉድ ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ አረጓዴነቷ ነው። የትም ብሆን አረንጓዴ ሥፍራና ዝናብ ሳይ ኢትዮጵያን እንድናፍቅ ያደርጉኛል። ባላፈው ሃዋይ ሄጄ በነበረ ጊዜ ከዝናብ በኋላ ያየሁት ጭቃው፣ ዛፎቹና ቀስተ ደመናው ኢትዮጵያን አስታውሶኝ ቆም ብዬ ፎቶግራፍ አነሳ ጀመር።

በቋሚነት በአንድ ቦታ ኖሬ ባላውቅም እንኳ የሰሜን አሜሪካ ሃገራትን ተመላልሼባቸዋለሁ። ኃይል ቢኖረኝ ሰሜን አሜሪካውያን ልዩነቶቻቸውን እንደ ሃብት ተጠቅመው እንደ አንድ ሕዝብ እንዲንቀሳቀሱ ባደርግ ደስ ባለኝ። የዘር፣ የቀለም፣ የኃይማኖት ... ብቻ ልዩነቶቻቸውን አንድ ማድረግ ቢችሉ. . .

Image copyright ALIOUNE FAYE
አጭር የምስል መግለጫ እንቁላል ከጥሬ ሳልመን ጋር ተደገርጎ የሚሠራውን ምግብ መመገብ እወዳለሁ

ሰሜን አሜሪካ ከኢትዮጵያ የሚለይዋት በርካታ ነግሮች አሉ። በተለይ ለሥራዬ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ነው መሰለኝ ከሁሉም በላይ ልዩነቱ የሚገለጽልኝ ስለቴክኖሎጂ ሳስብ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር ሳነፃጽረው በቴክኖሎጂ ልቀው እንደሄዱ ይሰማኛል።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ከሄድኩኝ ረዥም ጊዜ ቢሆነኝም ከወጣሁበት ጊዜ እስካሁን ብዙ ለውጦች እንዳሉ የሚነግሩኝ ጓደኞች አሉኝ። ለዚህም ነው ወደፊት ሥራዬን ወደ ኢትዮጵያ ከዚያም ደግሞ ለአህጉረ አፍሪካ ማድረስ የምፈልገው።

ብዙውን ጊዜ መንገድ ላይ ስለሆንኩኝ የኢትዮጵያን ምግብ ማግኘት ቀላል አይሆንልኝም፤ ቢሆንም ምንጊዜም ወደ ቫንኩቨር ስመለስ እናቴ ሠርታ ስለምትጠብቀኝ አልቸገርም። ያም ሆነ ይህ እኔ የቁርስ ሰው ነኝ።

የተመጣጠነና የምወደውን ምግብ ለቁርስ መመገብ ከምንም ነገር በላይ ያስደስተኛል። 'ኤግዝ ቤኔዲክት' የተሰኘውን እንደ እንቁላል ቁጭ ቁጭ ያለ ምግብ በጥሬ የሳልመን ዓሣ ከሆሎንዴዝ ማጣቀሻ ጋር ሁሌም ለቁርስ መመገብ ያስደስተኛል።

Image copyright ALIOUNE FAYE
አጭር የምስል መግለጫ ብዙውን ጊዜ በመስኮት የሚታየኝ ዕይታ

አብዛኛውን ጊዜዬን ከሃገር ሃገር በመጓጓዝ ስለሆነ የማሳልፈው የምወደው ዕይታ በአውሮፕላኑ መስኮት የሚስተዋለውን የደመና ግግር ነው። ከደመና በላይ ሆኜ ከደመና በታች ስላለው ማሰብ ያስደስተኛል።

እንደዚህ ዓይነት ሕይወት ብዙ ሰው የሚመኘው ሆኖም ግን ለሁሉም የማይሰጥ መሆኑን እረዳለሁ፤ ስለዚህ በጣምም ደስተኛ ነኝ። ይህን እንደወስን የሆንኩት በሕይወቴ ከባድ የምለው የመኪና አደጋ ካጋጠመኝ ወዲህ ነበር።

በመኪና መጓዝ በጣም ነበር የምወደው፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ እያልኩ እየነዳሁ ያላየሁት ሃገርና ከተማ የለም ። ነገር ግን አንድ ጊዜ ያጋጠመኝ አደጋ ብዙ ነገሮችን እንዳስብ ምክንያት ሆነኝ።

ቆም ብዬ ስለሕይወቴና ስለማንነቴ እንዳስብ ሆንኩኝ። በትንሽ ደቂቃ የሰው ልጅ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊቀየር እንደሚችልም ተገነዘብኩ። ስለዚህ ደስተኛ ሆኜ ለመኖር የሚያስደስተኝን ነገር መሥራት አለበኝ ብዬ በማሰቤ ነው የማይቋረጥና የሚቀያየር ኑሮ የተያያዝኩት።

በቅፅበት ካለሁበት ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ብችል እራሴን ከልጅነት ጓደኞቼ መካከል ባሳደገኝ ትምህርት ቤቴ ሊሴ ገብረ ማሪያም ግቢ ውስጥ ባገኘው እመኛለሁ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ካለሁበት 31፡ ''ብዙ ትውስታዎቼ ከዛፍና ከጭቃ አያልፉም''

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 32፡ "ኑሮን ፈታኝ የሚያደርገው ባህላቸው ነው"

ካለሁበት 33፡ ኑሮን በቴክኖሎጂ ምቹ ያደረገች ሃገር

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ