አዲስ ቋንቋ ለመማር አስበዋል? ለመሆኑ እድሜዎ ስንት ነው?

አዲስ ቋንቋ ለመማር አስበዋል? ለመሆኑ እድሜዎ ስንት ነው? Image copyright Getty Images

ቋንቋ መማርና እድሜ መሀከል ትስስር አይኖርም ብለው ለሚያስቡ፣ ቋንቋ ለመማር እድሜ መጠየቁ አስፈላጊ ላይመስላቸው ይችላል።

በቅርቡ ይፋ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ግን ከ10 ዓመት በኋላ አዲስ ቋንቋ መማር ከባድ ነው።

'ኮግኒሽን' የተሰኘው እውቁ የሳይንስ መፅሄት ላይ የተተየበ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ሰዎች ከ17 ወይም ከ18 አመታቸው በኋላ አዲስ ቋንቋ የመማር ችሎታቸው እያሽቆለቆለ ይሄዳል።

ጥናቱ የተሰራው በተለያየ እድሜና ሃገር የሚኖሩ 670 ሺህ ሰዎችን መሠረት አድርጎ ሲሆን፣ ተመራማሪዎቹ ማሳያ አድርገው የወሰዱት እንግሊዝኛ ቋንቋን ነበር።

ጥናቱ የተሰራው የእንግሊዝኛ ሰዋሰው ጥያቄዎች በፌስቡክ ተለጥፈው በተገኙ ምላሾቹን ሲሆን፣ የተጠያቂዎቹ እድሜና እንግሊዘኛ ቋንቋ በሚነገርበት ሃገር የቆዩበት ግዜ መጠን ከግምት ገብቷል።

አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ከ20 እስከ 30 ባለው የዕድሜ ክልል ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ የ10 አመትና የ70 አመት ሰዎችም የጥናቱ አካል ነበሩ።

በጥናቱ ከተሳተፉት ወደ 246 ሺህ ሚሆኑ እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩት ሁለትና ከዛም በላይ ቋንቋ ይችላሉ። ከነዚህ መካከል አፍ መፍቻቸው ጀርመንኛ፣ ሩስኪ፣ ቱርክኛና ሃንጋሪኛ የሆኑ ይገኙበታል።

ስ ቋንቋ የመማር ፈተና

ለጥናቱ በዋሉት የሰዋሰው ጥያቄዎች፣ ያለፈ ወቅትና ነባራዊ ሁኔታን የሚጠቁሙ አገላለፆች ተዋህደው፣ ምን ያህሉ ሰዎች ስህተቱን መለየት እንደሚችሉ ተፈትሿል።

ተመራማሪዎቹ ከጥናቱ ያገኙትን ውጤት ሲተነትኑ የተገነዘቡት ቋንቋ የመማር ችሎታ በልጅነት የላቀ ሲሆን፣ በወጣትነት ባለበት ደረጃ ቀጥሎ፣ እድሜ ሲገፋ ይቀዛቀዛል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፣ ዕድሜ እየጨመረ ሲሔድ አእምሮ አዳዲስ ነገር የመማር ብቃቱ እየተዳከመ ይመጣል። ምናልባትም ከ18 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎች አዲስ ቋንቋ ለመማር የሚከብዳቸው በዚህ ምክንያት ይሆናል።

Image copyright Getty Images

ሰዎች ከልጅነት ወደ ወጣትነት ከዛም ወደ ጉልምስና ሲያመሩ፣ ቋንቋ የመማር ብቃታቸው እየከዳቸው ይሄዳል።

የማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ተቋም የአእምሮና ኮግኒቲቭ ሳይንስ ምሁሩ ጆሽ ቴንባውም "የቋንቋ ትምህርት ከአካላዊ ለውጥ በተጨማሪ በማሕበራዊና ባህላዊ ተፅእኖ ስር ጭምርም ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

መምህሩ እንደሚሉት፣ ሰዎች 18 ዓመት ከሞላቸው በኋላ የትምህርትና የስራ ጫና ስር መሆናቸው በቋንቋ ትምህርት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።

ተስፋ አይቁረጡ. . .

የጥናቱ ውጤት ሙሉ በሙሉ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። በጎልማሳነት አዲስ ቋንቋ ለመማር መሞከር የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት። ለምሳሌ አዲስ ቋንቋ መማር የአዕምሮ መዋዠቅ (ዳይሜንሽያ) የመሰሉ ህመሞችን እንደሚከላከል ጥናቶች ያሳያሉ።

ለዮርክ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ መምህሩ ፕሮፌሰር ማርሊን ቪላሚን፣ አዲስ ቋንቋ ለመማር የግድ በልጅነት መጀመር ያሻል የሚለው መላ ምት ውሃ አይቋጥርም።

"በ20 ዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎች አዲስ ቋንቋ ተምረው ለስለላ የተላኩባቸው ሁኔታዎች አሉ። አዲስ ቋንቋ ለመማር የዕድሜ ገደብ አለ ብዬ አላስብም። ችሎታው ከሰው ሰው የተለያየም ነው" ይላሉ።

ሌላው የቋንቋ ምሁር ዶ/ር ዳንጂላ ጣሪክ፣ ጥናቱ በሰዋሰው ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ ክፍተት እንደሚፈጥር ገልፀው፣ የሰዋሰው ችሎታቸው ደካማ ሆኖ፣ ጥሩ ተናጋሪዎች እንዳሉ ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች