የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ

የሙዚቃ ህክምና Image copyright Getty Images

ሙዚቃ ጥበብ ነው፤ ስሜት ያድሳል፤ ሕመምን ይሽራል። እንኳን ሰው እንስሳትና እፅዋት በሙዚቃ ይደሰታሉ። ለዚህም ነው ያደጉት አገራት ሙዚቃን አንደ አንድ የሕመም መፈወሻ መድሃኒት እየተጠቀሙበት ያለው።

ታዲያ ይህ የሕክምና ጥበብ ወደ እኛ አገርም ተሻግሯል። አሻጋሪው ደግሞ ዶክተር መልካሙ መዓዛ ናቸው።

ሙዚቃ ሳይሰሙ መወዛዋዝ ይችላሉ?

ሙዚቃን ለሰላም

በቅዱስ ያሬድ ዘመን ሰዎች ሙዚቃና ቅዳሴን በመጠቀም የታመመ ሰውን ስቃይ በመቀነስ ለታማሚው ምድራዊ ገነትን ለመፍጠር ሲጠቀሙበት እንደነበር በማውሳት ይጀምራሉ - ዶ/ር መልካሙ። በህዳሴ ዘመን ደግሞ የሙዚቃ ሐኪሞች የስሜታችንና የሰውነታችን ተፈጥሯዊ ለውጦችን ለማምጣት ሙዚቃን ለሳይንሳዊ ጥናት እንደተጠቀሙበት ያስረዳሉ።

"አሁን ወዳለንበት ክፍለ ዘመን ስንመጣ፤ ሙዚቃና ሕክምና በጣም የተሳሰሩበት በተለይ በምዕራባውያን የጤና ተቋማት ውስጥ ሙዚቃን እንደ ደጋፊ የሕክምና ግብዓት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ" የሚሉት ዶክተር መልካሙ ሙዚቃ ጤናን አስቀድሞ ለመጠበቅ እና ከህመም ለመዳን አስተዋፅዖው ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ።

ዶክተር መልካሙ የሙዚቃ አድናቂ ናቸው። ክራር፣ ጊታር፣ ፒያኖና ቶም የተባሉ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫዎታሉ። ድፕ አቢሲኒያ (ትራይባል ማጂክ) የተሰኘ የሙዚቃ አልበምም አሳትመዋል።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መልካሙ የሙዚቃ ዝንባሌ ያደረባቸው ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በግላቸው ያጋጠማቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ተሞክሯቸውን ለቢቢሲ እንዳጋሩት፤ በሥራቸውና በቤተሰባቸው አካባቢ ችግር ገጥሟቸው ለጭንቀት ተዳርገው ነበር፤ ከዚያም ወደ ሙዚቃ ቀረቡ። የሚነጋገሩትም የሚያዋዩት ሙዚቃን ሆነ። በጊዜ ሒደትም ከገቡበት ስሜት እየተላቀቁ መጡ።

በራሳቸው ላይ ለውጥ ካዩ በኋላ ለሌላው ሰው ለመትረፍ አብዝተው ማሰብ ጀመሩ፤ በምዕራቡ ዓለም የተለመደውን የሙዚቃ ሕክምና ሳይንስን ለማጥናትና ዘርፉ ላይ ለመስራት ወሰኑ።

የሙዚቃ ሕክምና እንዴት ይሰጣል?

ዶ/ር መዓዛ የሙዚቃ ሕክምና የሚሰጥባቸውን ሁለት መንገዶች ያብራራሉ። የሙዚቃ ሕክምና በተቋማት ያሉ ባለሙያዎች ሙዚቃን በመጠቀም ደጋፊ ወይም አማራጭ ሕክምና የሚሰጡበት ዘዴ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የሙዚቃ ሕክምና ነው።

በማሕበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የሙዚቃ ሕክምና በማከም ሳይሆን በመከላከል ደረጃ የሚሰጥ ነው። የሕክምናው ዓይነቱም በየቤቱ ታመው የተቀመጡና ማህበረሰቡ ጋር የማይቀላቀሉ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት እንደሆነ ያብራራሉ።

አሁን ግን የጥናት ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ሕክምናው ከሌሎች የሕክምና ሙያ ዓይነቶች ጋር ተቀናጅቶ እየተሰጠ መሆኑንም ያክላሉ።

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

የሙዚቃ ህክምናው የእድሜ ገደብ የለውም፤ ለህፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች ይሰጣል። በተለይ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት፣ የባህሪ ችግር፣ የአካል ጉዳት፣ የስሜት መረበሽ፣ የመናገር፣ ማየትና መስማት ለተሳናቸው፣ የነርቭ እክል ላጋጠማቸው፣ የቀዶ ህክምና ላደረጉ፣ ለካንሰር ህሙማን፣ የአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ ተጠቂ ለሆኑ፣ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው እንዲሁም የአመጋገብ ችግር ላለባቸው ይሰጣል።

በተጨማሪም ለእናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ ወቅት እንዲሁም ከወሊድ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ህክምናው ሊሰጥ ይችላል ።

ሙዚቃ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ ዶፓሚንና ሴሮቶኒን የተባሉ ሆርሞኖች በተለያየ ሁኔታ እንዲመነጩ ስለሚያደርግ በሰው ልጆች ተግባቦት፣ ማህበራዊ መስተጋብር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የስሜት ህዋሳት፣ የሥነ-ልቦናና የስሜት ለውጥ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ።

ሕክምናው በዋናነት በግል ወይም በቡድን የተቀዳን ሙዚቃ አሊያም የሙዚቃ ሐኪሞች የሚጫወቱትን ማዳመጥ፣ ማንጎራጎር፣ በግል ወይም በቡድን ሐኪሙ በሚያዘው መሰረት ሙዚቃን መጫወት እና የምት (ሪትም) እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያካትት ዶክተሩ ተናግረዋል።

የሚያክሙን ሙዚቃዎች ዓይነት

ዶክተር መልካሙ እንደገለፁልን ለሙዚቃ ሕክምና የትኛውም ዓይነት ሙዚቃ ጥቅም ላይ አይዉልም። ከዚያ ይልቅ ታካሚው ላጋጠመው የህመም ዓይነት የተዘጋጁ የሙዚቃ ዓይነቶች ያስፈልጋል።

ከእነዚህም መካከል ቀደም ብለው የተቀዱ ሙዚቃዎች አሊያም ሐኪሙ በቀጥታ ለታካሚው የሚጫወታቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

''እነዚህ ሙዚቃዎች ታካሚው እንዳለበት የህመም ዓይነትና እንደሚያስፈልገው ሕክምና በምት፣ በቅጥነት፣ በውፍረት፣ በፍጥነት፣ በድምፅ ከፍታና በተለያዩ ሁኔታዎች ሊዘጋጁ ይችላሉ፤ በገበያ ላይ ከምናውቃቸው ሙዚቃዎች ውስጥ በአብዛኛው ክላሲካል የሚባሉት ሙዚቃዎች ለሕክምና ይውላሉ" ይላሉ ዶክተር መልካሙ።

የሞዛርትንና የቤትሆቨንን ሙዚቃዎች በመጥቀስ ቆየት ባለው ጊዜ የነበሩት ረቂቅ (ክላሲካል) ሙዚቃዎች በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፉ ሙዚቃዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ከድምፃዊት ቤቲ ጂ እና ቸሊና ጀርባ

ዝነኛው ኤርትራዊ ድምጻዊ የማነ ባርያ ሲታወስ

ባለሙያው እንደሚሉት ጤና ላይ አዎንታዊ ውጤት ያላቸው ሙዚቃዎች እንዳሉ ሁሉ ጤናን የሚያውኩ ሙዚቃዎችም አሉ። እነዚህም ሙዚቃዎች በአጠቃላይ ጠንካራ ምት፣ ንዝረትና ፍጥነት ያላቸው እንደ ሮክ፥ ድራም፥ ባዝና ትራንስ ያሉ የሙዚቃ ዓይነቶች ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች አመልክተዋል።

በሰው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ እነዚህ ያሉ ሙዚቃዎች የሚሰሙበት አካባቢ ያሉ ዕፅዋቶች ሳይቀሩ እድገታቸው እንደሚቀጭጭ ጥናቶችን ያጣቅሳሉ።

የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ

ሳይንሳዊ የሆነው የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ ገና በጅማሮ ላይ ያለ ነው። ከቅርብ ዓመታት በፊት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሙዚቃ ሕክምናን የሚመለከት አንድ የሥራ ሂደት ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፁልን ዶክተር መልካሙ መዓዛ፤ በገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያና ማከሚያ ማዕከል ውስጥ በሳምንት ለሦስት ቀናት የሙዚቃ ሕክምና በተለይ የምት እንቅስቃሴ ሕክምና መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል።

የማይክል ጃክሰን "የአፍጢም ዳንስ" ምሥጢር

ይሁን እንጂ እንደ ሌሎች ሕክምናዎች ሁሉ የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያ ቢያስፈልገውም በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች ባለመኖራቸውና በሌሎች ወቅታዊ ምክንያቶች ውጤቱ አርኪ እንዳልነበር ይገልፃሉ።

ቢሆንም ግን የተጀመረው እንቅስቃሴ ሕክምናውን ለማስጀመርና በሰዎች ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረገ ጥረት እንደሆነ ያምናሉ። እርሳቸው እንደሚሉት እንቅስቃሴው የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያን ከውጭ አገር በማስመጣት ድጋፍ እንዲገኝም መንገድን አመቻችቷል።

እንግሊዝ አገር ከሚገኝ 'ሚዩዚክ አዝ ቴራፒ' ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በተፈጠረ ግንኙነት የሙዚቃ ሕክምና በባለሙያ የሚታገዝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ዶክተር መልካሙ ነግረውናል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ