የሕንድ የአቧራ አውሎ-ንፋስ 125 ሰው ቀጠፈ

የሕንድ የአቧራ አውሎ-ንፋስ 125 ሰው ቀጠፈ Image copyright AFP

በሰሜናዊው የሕንድ ክፍል ትናንት የተከሰተ የአቧራ አውሎ ንፋስ እሰካሁን ቢያንስ የ125 ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ሊታወቅ ችሏል። አውሎ-ንፋሱ ተጨማሪ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል አሁንም ስጋት አለ።

መብረቅ ቀላቅሎ በፍጥነት እየተጓዘ ያለው ይህ አውሎ ንፋስ የበርካታ ሰወችን ቀዬ ከጥቅም ውጭ ያደረገ ሲሆን ጉዳትም የደረሰባቸው ሰዎች የትየለሌ እንደሆኑ ታውቋል።

አንድ በአካባቢው የነብስ ማዳን ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ ሰው እንደተናገሩት መሰል ክስተት የተመዘገበው ከ20 ዓመት በፊት ሲሆን የአሁኑ ግን እጅግ በጣም አስከፊ ጥፋት እያደረሰ ነው። አክለውም የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የሕንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ድርጅት በሳምንቱ መጨረሻ አውሎ ንፋሱ ክልሉን እያሰፋ ሊቀጥል ይችላል ሲል ተንብይዋል። "ሰዎች ነቅተው ይጠብቁ ዘንድ ይሁን" ሲልም ተደምጧል።

ኡታር ፕራዴሽ እና ራጃስታን በተባሉት የሕንድ ሰሜናዊ ክፍል ግዛቶች የተከሰተው ይህ አውሎ ንፋስ የኮረንቲ ገመዶችን ከመበጣጠሱም ባሻገር ዛፎች ነቅሏል፤ እንዲሁም የበርካታ የቤት እንስሳት ሕይወትንም ቀጥፏል።

Image copyright LAXMIKANT PACHOUR

ታዋቂው የታጅ መሃል ቤተ-መንግሥት የታነፀባት የአግራ ግዛትም በአውሎ ንፋሱ ከተመቱ አካባቢዎች አንዷ መሆኗም ይዘገብ ይዟል።

ከሟቾቹ አባዛኛዎቹ በተኙበት ቤት የተደረመሰባቸው ሰዎች ሲሆኑ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬድራ ሞዲ በደረሰው ጥፋተ እጅግ ማዘናቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

የኡታር ፕራዴሽ አስተዳደር ካሳ ይሆን ዘንድ 400 ሺህ ወይንም 6 ሺ ዶላር ገደማ ገንዘብ የሕንድ ሩጲ ለሟች ቤተሰቦች አለግሳለሁ ሲል ገልጧል።