ቢል ኮዝቢና ፖላንስኪ ከኦስካር አካዳሚ ተባረሩ

ቢል ኮዝቢና ፖላንስኪ ከኦስካር አካዳሚ ተባበሩ Image copyright Reuters/EPA

የፊልሙ ዘርፍ ፈርጦች የሚሞገሱበትን የኦስካር ሽልማት የሚያዘጋጀው 'ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስ' የተሰኘው ተቋም ተዋናዮቹን ያባረራቸው የድርጅቱን መርህ ተከትሎ መሆኑን አሳውቋል።

በተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ የሚታወቀው ጥቁር አሜሪካዊው የጥበብ ሰው ቢል ኮዝቢ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል በሚል እሥር የተፈረደበት ባለፈው ወር ነበር። የፊልም አዘጋጅና የኦስካር አሸናፊው ሮማን ፖላንስኪ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1977 የ13 ዓመት ታዳጊን አስገድዶ መድፈሩን አምኗል።

የቢቢሲው ጄምስ ኩክ እንደዘገበው፣ ኮዝቢና ሮማን ከኦስካር ባለሟልነት ስለመባረራቸው ያሉት ነገር ባይኖርም፣ የኮዝቢ ባለቤት ካሚሌ "ፍርዱ ትክክለኛ አይደለም" ብላለች።

ሮማን ጥቃት ማድረሱን ካመነ በኋላ ተቋሙ በአፋጣኝ አለማባረሩ፣ የተቋሙን ቦርድ አባላት በማህበራዊ ድረ ገፅ ሲያስተቻቸው ነበር።

የወሲባዊ ጥቃት ክሶች የሆሊውድን መንደር የናጡት በቢል እና በሮማን ጉዳይ ብቻ አይደለም። በርካታ ሴቶች የወነጀሉት ፕሮዲውሰሩ ሀርቪ ዋንስታይንም ይገኝበታል። ባለፈው አመት ሀርቪም ከኦስካር አካዳሚ መባረሩ ይታወሳል።

ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕ ለማግኘት #MeToo ወይም 'እኔም' የተሰኘ ንቅናቄ ጀምረዋል። ንቅናቄው ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አደባባይ ወጥተው አጥቂዎቹን ለመክሰስ ድፍረት እንዲያገኙ ያበረታታል።

ንቅናቄው ሀርቪ ዋይንስታይንን የመሳሰሉ የሙያና የገንዘብ ጉልበታቸውን ተጠቅመው በርካታ ሴቶችን ያጠቁ ወንዶችን ለፍርድ በማቅረብም ቀጥሏል።

ኮዝቢና ሮማን ከኦስካር አካዳሚ የተባረሩበት ውሳኔ

የኦስካር አካዳሚ የቦርድ አባላት ለሁለት ቀናት ውይይት ካደረጉ በኋላ ነበር ከውሳኔ የደረሱት።

አባላቱ ውሳኔውን ትላንት ሲያስተላልፉ "ቦርዱ ኮዝቢና ሮማንን ከአካዳሚው አባልነት የሰረዛቸው የተቋሙን ህግጋት ተከትሎ ነው። አባላት የቦርዱን ደንብ ከማክበርም ባሻገር የሰዎችን ሰብአዊ መብት እንዲያከብሩ እንሻለን" በማለት ነበር።

ባለፉት 91 ዓመታት ተቋሙ በአራት ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዷል። እ.አ.አ 2004 ላይ ተዋናዩ ካርሚን ካርዲ ለህዝብ ዕይታ ያልበቃ ፊልም ለጓደኛው በመላኩ ተባሯል።

በሮማን ላይ የተወሰደው እርምጃ መዘግየት

የ84 አመቱ ፀሐፊ፣ አዘጋጅና ተዋናይ ሮማን፣ ሳማንታ ጌሚር የተባለች ሴትን አስገድዶ መድፈሩን ካመነ አራት አስርታት ተቆጥረዋል። በወቅቱ ፈረንሳይ-ፖላንዳዊው ሮማን የታሰረው ለ42 ቀናት ብቻ ነበር።

ከአሜሪካ ወደ ፈረንሳይ ሸሽቶ ፍርዱን ካመለጠ በኋላ ዳግም አልተመለሰም። የአሜሪካ መንግስት ለማስመለስ ያደረገው ጥረትም በፈረንሳይና ፖላንድ እምቢተኝነት ሳብያ ከሽፏል።

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2010 ሮማንን ከስዊዘርላንድ ወስዶ ለፍርድ ለማቅረብ ያደረገችው ጥረት ባይሳካም፣ ለዘጠኝ ወር ከቤት ያለመውጣት (ሀውስ አረስት) ተፈርዶበታል።

ጥቃቱ የደረሰባት ሳማንታ፣ ለአሜሪካ ፍርድ ቤት "ይቅር ብዬዋለሁ፣ ክሱን ይቋረጥና በሰላም ልኑር" ብትልም ተቀባይነት አላገኘችም።

ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ሮማን ለ40 ዓመታት ከኦስካር አካዳሚ አለመባረሩ ጥያቄ አጭሯል።

"የ13 አመት ታዳጊ ተደፍራ፣ ሮማንም ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ እርምጃ አለመወሰዱ፣ ተቋሙ ሰብአዊ መብት ስለማክበሩ ጥያቄ ያስነሳል" ተብሎም ተወንጅሏል።

ከስምንት ሺ በላይ አባላት ያሉት ተቋሙ፣ በቅርቡ መተዳደርያ ደንቡን ቢያሻሽልም ከወቀሳ አላመለጠም። #MeToo የተሰኘውና ሌሎችም ንቅናቄዎች የፊልም ዘርፉን ጥላሸት ቀብተውታል።

ከፍርዱ በኋላ የተባረረው ኮዝቢ

የ80 ዓመቱ ቢል ኮዝቢ ወንጀለኛ ሆኖ የተገኘው በሶስት የወሲባዊ ጥቃት ክሶች ነው። እያንዳዳቸው የአስር አመት እስራት ያስፈርዱበታል።

እ.አ.አ በ2004 የቀድሞዋ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች አንድርያ ኮንስታንድ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ በማድረሱ ተከሷል። ፍርድ ቤቱ ከውሳኔ ሳይደርስ ነበር ሁለተኛ ክስ የተከተለው።

ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስ፣ ቢልን ከኦስካር አካዳሚ ያባረረው የእስር ፍርድ እንደተበየነበት ነው።

"ዘ ኮዝቢ ሾው" የተሰኘው አስቂኝ የቴሌቭዠን ድራማ ላይ ቢል አባት ሆኖ ሲተውን፣ "የአሜሪካ አባት" የተሰኘ የአክብሮት ቅፅል ስም አትርፎ ነበር። በወቅቱ በአሜሪካ ቁጥር አንድ ተከፋይም ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች