በሞያሌ ትናንት በተከሰተ ግጭት የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

ከኢትዮጵያ ሞያሌ የተፈናቀሉ ሰዎች፤ መጋቢት 2010 Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ከኢትዮጵያ ሞያሌ የተፈናቀሉ ሰዎች፤ መጋቢት 2010

ግጭቱ የተከሰተው በአካባቢው ባሉ የሶማሌና የኦሮሞ ነዋሪዎች መካከል እንደነበር የሚናገሩት የዓይን እማኞች በርካቶች በመሸሽ ወደ ኬንያ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ከሞያሌ እና ያቤሎ ሆስፒታል ምንጮች ማረጋጋጥ እንደቻልነው በትናንትናው ግጭት ብቻ ቢያንስ 10 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የቦረና ዞን የጤና ቢሮ ሃላፊ ሆኑት አቶ ሮባ ዴንጌ እንዳሉት ከሆነ በትላንቱ ግጭት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሞያሌ ሆስፒታል ከተወሰዱ 50 ሰዎች መካከል 8ቱ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የያቤሎ ሆስፒታል ተጠሪ የሆኑት አቶ አሬሮ ቢቂቻ ደግሞ ወደ ያቤሎ ሆስፒታል ሪፈር ተብለው ከተላኩ 11 ሰዎች መካከል ሁለት የጸጥታ አስከባሪ አባላት ህይወታቸው ማለፉን ይናገራሉ።

በሞያሌ ከተማ የኮማንድ ፖስቱ አዛዥ ሆኑትን ጀነራል ጌታቸው ጉዲናን ስለተከሰተው ግጭት ማብራሪያ እንዲሰጡን ብንጠይቅም የተሟላ መረጃ የለኝም በማለት አስተያየታቸውን ሊሰጡን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ 'በሞያሌ በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ ነው' ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኃላፊነት የተሰጠዉ አካልም አስፈላጊውን እርምጃ ወስዶ ጉዳቱን ከወዲሁ ማሰቆም አለበት ሲሉ በአጭር መልዕክታቸው አሳስበዋል፡፡

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ