ኢቦላ ዳግም አገረሸ

የጤና ሠራተኛ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ መቆጣጠሪያ ልዩ ክልል ሲንቀሳቀስ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ለመጨረሻ ጊዜ የኢቦላ ወረርሽኝ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው በ2017 ሲሆን አራት ሰዎችን ገድሏል

በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኢቦላ ዳግም ማገርሸቱ የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አስታወቀ።

ኢቦላ መመለሱ የታወቀው በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ የ17 ሰዎች ሞት ከተሰማና የሁለቱ ሞት በኢቦላ ቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

ቦኮሮ በተባለችው ከተማ የተከሰተው ይህ ወረርሽኝ ዳግም የተከሰተው በአገሪቱ አራት ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ከሞቱ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2014 በተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በጊኒ፣ በሴራሊዮን እና በላይቤሪያ ብቻ አስራ አንድ ሺህ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩት የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስታወቀው የኢቦላ ዳግም ማገርሸት የተረጋገጠው ከአምስት ታማሚዎች በሁለቱ ላይ ናሙና ተወስዶ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ነው።

"ከአጋሮቻችን ጋር በቅልጥፍናና በተቀናጀ መልኩ በመሥራት በጊዜ የበሽታውን ሥርጭት መግታት ይኖርብናል" ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፒተር ሰላማ።

ድርጅቱ አንድ ሚሊዮን ዶላር ከአስቸኳይ ጊዜ ፈንድ ወጪ በማድረግና 50 የጤና ባለሞያዎችን ወደ ሥፍራው በማሠማራት ምላሽ መስጠቱንም አሳውቋል።

በኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ ይህ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው።

ቫይረሱ ለመጀመርያ ጊዜ በአገሪቱ የተገኘው እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ አቆጣጠር በ1976 ሲሆን ያን ጊዜ አገሪቱ ዛየር በሚል ስም ትጠራ ነበር።