የዛምቢያ ዩኒቨርስቲ ይቅርታ ጠየቀ

ተማሪ ዲኪና ሙዘያ Image copyright Dikina Muzeya
አጭር የምስል መግለጫ ተማሪ ዲኪና ሙዘያ እንደምትለው ወንድ ተማሪዎች የሴት ተማሪዎች ገላ ላይ ሳይሆን ንባባቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል

ከሰሞኑ ሴት ተማሪዎቹን "ወንድ ተማሪዎች ማጥናት አልቻሉምና እየተራቆታችሁ ቤተመጻሕፍት አትምጡ " ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቶ የነበረው የዛምቢያ ዩኒቨርስቲ በይፋ ይቅርታ ጠየቀ።

ዩኒቨርስቲው እንዳለው ወጥ የሆነ የተማሪዎች የአለባበስ መመሪያ እንደሌላውና አውጥቶት የነበረው ማሳሰቢያ "ያረጀና ያፈጀ፣ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት፣ የወግ አጥባቂዎች ኋላ ቀር አመለካከት ነው" ካለ በኋላ ይህ ዓይነቱን አመለካከት እንደማይታገስ አስታውቋል።

በሉሳካ የሚገኘው የዛምቢያ ዩኒቨርስቲ በቤተ መጻሕፍቱ በር ላይ ሰቅሎት የነበረው ጽሑፍ "ጨዋ አለባበስ መርሃችን ነው" የሚል ነው።

በተጨማሪም ጽሑፉ ሴት ተማሪዎቹን "ግማሽ እርቃን አለባበሳችሁ ወንድ ተማሪዎችን ከጥናታቸው እያስተጓጎለ ስለሆነ አጫጭር ቀሚሶችን ከመልበስ ተቆጠቡ" የሚል ይዘት ነበረው።

ይህ ክስተት በአመዛኙ ወግ አጥባቂ የሆነችውን ዛምቢያን በሁለት ጎራ ከፍሏታል።

ብዙዎች የሴቶች አለባበስ ገደብ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ ሌሎች ደግሞ አለባበሳችንን ሳይሆን ስሜታችሁን አደብ አስገዙ ሲሉ ይከራከራሉ።

የዩኒቨርስቲው የቤተ መጻሕፍት ኃላፊ ክሪስቲን ካኒየንጎ ይቅርታ በጠየቁበት ደብዳቤ እንዳሉት ቀደም ሲል የተሰቀለው ጾታን የለየ ማሳሰቢያ የዩኒቨርስቲውን አመራር የሚወክል አይደለም።

"ያለምንም ማቅማማት የቤተ መጻሕፍታችንን ሴት ተጠቃሚዎች ከልባችን ይቅርታ መጠየቅ እንሻለን። ሴት ተማሪዎቻችን ቤተ መጻሕፍቱን ሲጠቀሙ በሙሉ መተማመንና ምቾት እንዲሆን እንፈልጋለን" ያሉት ክሪስቲን ካኒየንጎ በተጨማሪም

"መከባበርና ብዘኃነት የዩኒቨርስቲያችን የማዕዘን ድንጋይ ነው" ብለዋል ሚስ ካንየንጎ የቢቢሲው ኬኔዲ ጎንድዌ ትዊት ባደረገው ይፋዊ የይቅርታ ደብዳቤ።

በትናንት ዘገባችን የቤተ መጻሕፍቱን የአለባበስ ክልከላ ተችታ የነበረችው የሦስተኛ ዓመት ተማሪዋ ዲኪና ሙዘያ ዩኒቨርስቲው ይቅርታ መጠየቁን ተቀብላዋለች።

"ለወደፊቱ የዩኒቨርስቲው ቤተ መጻሕፍት በሚያወጣቸው ማሳሰቢያዎች ላይ ጾታን ለይቶ ከሚሰነዘሩ አስተያየቶች ራሱን ማራቅ አለበት"ትላለች ሙዘያ።

በተቃራኒው የዩኒቨርስቲው ወንድ ተማሪ ኪሊዮን ፊሪ በአለባበስ ላይ እገዳ የሚጥለውን ማሳሰቢያ ደግፎት ነበር።

"እንዴት ነው አንዲት ሴት በአጭር ቀሚስና የሰውነቷን ቅርጽ በሚያጎላ ሱሪ (ታይት) ስታልፍ እያየህ ጥናትህ ላይ ማተኮር የምትችለው?" ሲል መናገሩ ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች