በማሌዢያ ምርጫ የ92 ዓመቱ አዛውንት አሸነፉ

ሞሐቲር ሞሐመድ Image copyright Reuters

የማሌዢያ ምርጫው ፍጹም ያልተጠበቁ ውጤቶች የታዩበት ነበር።

ለ60 ዓመታት በሥልጣን የቆየ አውራ ፓርቲ ተሸንፏል። ከጡረታ በኋላ ወደ ፖለቲካ የተመለሱ ሰው አሸንፈዋል።

አዲሱ ተመራጭ ከጡረታ መመለሳቸው ብቻም ሳይሆን በዕድሜ የዓለም አዛውንቱ ተመራጭ መሪ በመሆን አገሪቱን በአዲስ የታሪክ መዝገብ እንድትሰፍር አድርገዋል።

ምርጫውን ያሸነፉት የቀድሞ የማሌዢያ የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የ92 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሞሐቲር ሞሐመድ ናቸው።

ሞሐቲር ጡረታ ከወጡ በኋላ ድንገት ተመልሰው የተቃዋሚ ፓርቲን በመቀላቀል ለዚህ ያልተጠበቀ ድል መብቃታቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

ይህ ታሪካዊ የተባለለት ድል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1957 ጀምሮ የሥልጣን መንበሩን ተቆጣጥሮት የነበረውን የባሪሲያን ናሲዮናል ጥምረት የተሰኘውን ገዢ ፓርቲ ከጨዋታ ውጭ አድርጎታል።

ሞሐቲር እንዳሉት ፓርቲያቸው የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ጠንክሮ ይሠራል።

ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚስተር ናጂብ እንስካሁን በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም።

ድሉ ከተሰማ ከደቂቃዎች በኋላ ሞሐቲር ለደጋፊዎቻቸው እንደተናገሩት ፓርቲያቸው ያሸነፈው "ጥቂት ድምጾችን በማግኘት፣ ወይም አነስተኛ መቀመጫ በማግኘት ሳይሆን በሰፋ ልዩነት ነው።"

ይፋ የተደረገው የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው ተቃዋሚው ፓካታን ሃራፓን ወይም አሊያንስ ኦፍ ሆፕ ከ222 የምክር ቤት መቀመጫዎች 113ቱን ወስዷል። ተሸናፊው ባሪሲዮን ናሲዮናል ደግሞ 79 መቀመጫዎችን ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው።

የበዓለ ሲመቱ ሥነ-ሥርዓት የፊታችን ሐሙስ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጋዜጠኞች የተናገሩት እኚህ አዛውንት መሪ ለደጋፊዎቻቸው የሁለት ቀናት የፌሽታ ቀንን አውጀዋል።

በአንድ አውራ ፓርቲ አመራር ሥር ዕድሜያቸውን የጨረሱ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለጽ በዋና ዋና ከተማዎች አደባባይ ወጥተው ታይተዋል።

አሸናፊው አዛውንት በቀድሞው ገዢ ፓርቲ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለ22 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በ2003 ነበር ይህንኑ ሥልጣናቸውን የለቀቁት።

እርሳቸው በአመራር በነበሩበት ዘመን ማሌዢያ በኢኮኖሚ እድገቷ "የእስያ ታይገሮች" ከሚባሉ አገሮች ተርታ ትመደብ ነበር ተብሏል።

"የእስያ ታይገሮች" በመባል የሚታወቁት አገራት በ1990ዎቹ ከፍተኛ የምጣኔ ሐብት ግስጋሴን ያሳዩ ናቸው።

ተያያዥ ርዕሶች