ሰሜን ኮሪያ ሦስቱን አሜሪካዊያን ከእስር ፈታች

ከግራ ወደ ቀኝ፤ ኪም ሃክ ሶንግ፥ ኪም ዶንግ ቹል፣ ቶኒ ኪም Image copyright Reuters / AFP
አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ወደ ቀኝ፤ ኪም ሃክ ሶንግ፣ ኪም ዶንግ ቹል፣ ቶኒ ኪም

ዋይት ሃውስ የሦስቱ አሜሪካዊያን ከእስር መፈታት እንደ መልካም እርምጃ ወስዶታል።

ኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ተገናኝተው ውይይት ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ሦስቱ ኪሞች መፈታታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት መልክ ለማስያዝ ፍላጎት እንዳለ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።

ሁለቱ መሪዎች የት እንደሚገናኙ እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

ዶናልድ ትራምፕ ግን "በቀጣይ ሦስት ቀናት የምንገናኝበት ቦታ ይፋ ይደረጋል" ብለዋል።

"ከልብ የመነጨ ምስጋናችንን ለዶናልድ ትራምፕ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖምፔዮ እናቀርባለን" ብለዋል ሦስቱ አሜሪካዊያን።

"አምላክን፣ ቤተሰቦቻችንና ለኛ ሲጸልዩ የነበሩ ወዳጆቻችንን ሁሉ እናመሰግናለን" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ሦስቱ አሜሪካዊያን ሰሜን ኮሪያን አደጋ ላይ በሚጥል እንቅስቃሴ ውስጥ ነበሩ በሚል በሰሜን ኮሪያ በግዞት ቆይተዋል።

የመፈታታቸው ዜና የተሰማው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፖምፔዮ ስለመጪው የኪምና የትራምፕ ውይይት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ፕዮንግያንግ በገቡበት ወቅት ነበር።

"ኪም ጆንግ ኡን ዜጎቻችን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መፍቀዳቸውን አደንቃለሁ" ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ።

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ጨምረው እንዳሉትም "ሦስቱን አሜሪካዊያን በዋሺንግተን አንድሩ አየር ኃይል ማረፊያ ሄጄ በግሌ አቀባበል አደርግላቸዋለሁ" ብለዋል።

ኪም ጆንግ ኡን በበኩላቸው አሜሪካ ያቀረበችውን የይፈቱልኝ ጥያቄ ተቀብለው ለሦስቱ ሰዎች ምህረት ማድረጋቸውን የኮሪያ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሦስቱ አሜሪካዊያን እነማን ነበሩ?

የመጀመርያው ኪም የታሰረው በ2015 ሲሆን የተቀሩት ሁለቱ ግን በእስር የቆዩት ላለፈው አንድ ዓመት ብቻ ነው።

  • ኪም ሃክ ሶንግ በግንቦት 2017 ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው። የክርስቲያን ሚሲዮናዊ እንደሆነና በፕዮንግ ያንግ ዩኒቨርስቲ የሳይስንና ቴክኖሎጂ ለምርምር የሚሆን እርሻ ለመጀመር ዕቅድ እንደነበረው ተነግሯል።
  • ኪም ሳንግ ዱክ እንዲሁ በፕዮንግያንግ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውስጥ ይሠራ እንደነበረና በታኅሳስ 2017 አገር በመሰለል ወንጀል ተከሶ እንደነበር ተዘግቧል። የደቡብ ኮሪያ ሚዲያ እንደሚለው ግን ሰውየው በሰብአዊ ተግባር ተሠማርቶ የቆየ ነው።
  • ኪም ዶንግ ቹል በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ሰባኪ ሲሆን በ2015 ነበር በስለላ ተግባር ተሰማርተሃል በሚል በቁጥጥር ሥር የዋለው። የ10 ዓመታት እስርና ግዞት ፍርደኛም ነበር።

በሰሜን ኮሪያ ከ120ሺህ በላይ እስረኞች እንደሚገኙ "የሰብአዊ መብት በሰሜን ኮሪያ" የተሰኘ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሪፖርት ያሳያል።

ሰዎች በዚያች አገር ለእስር የሚዳርጋቸው ነገር በግልጽ ይህ ነው የሚባል እንዳልሆነና በርካቶች የደቡብ ኮሪያን ዲቪዲ በመመልከታቸው ብቻ ለእስር ይዳረጋሉ ይላል ሪፖርቱ።

ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመሻገር ሞክራችኋል በሚል በእስር ቤት የሚማቅቁም በርካቶች ናቸው።

እስረኞችን በከባድ የጉልበት ሥራ መቅጣት በሰሜን ኮሪያ የተለመደ ተግባር ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ