በጉጂ እና ጌዲዮ ግጭት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቀሉ

ጉጂ-ጌዲዮ Image copyright OCHA

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ዘገባ እንደሚያመለክተው በምዕራብ ጉጂ እና በጌዲዮ ዞኖች አዋሳኝ ድንበር ላይ በተከሰተ ግጭት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ትናንት ይፋ የሆነው የኦቻ ዘገባ እንደሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ጥቂት አጋሮች አነስተኛ ድጋፍ አድርገዋል፤ ይሁን እንጂ ከተፈናቃዮቹ ቁጥር እና ፍላጎት አንጻር የተደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ሚያዝያ 5 በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ ድንበር ላይ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ እንዲሁም ንብረት ወድሟል።

ወደ 200 ሺህ ይጠጋሉ ከተባሉት ተፈናቃዮች መካከል 100 ሺህ የሚሆኑት ከጌዲዮ ዞን የተፈናቀሉ ሲሆኑ የተቀሩቱ ደግሞ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ ናቸው ሲል ዘገባው ያትታል።

ቀያቸውን ጥለው ከተሰደዱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የሁለቱ ክልል መሪዎች ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ የተስማሙ ሲሆን እስካሁን ወደ 85 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው የተመለሱ ሲሆን በርካቶች ግን ለደህንነታቸው በመስጋት ለመመለስ እስካሁን ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ዘገባው አክሎ ይጠቁማል።