ሁለቱ አወዛጋቢ መሪዎች በሲንጋፖር ይገናኛሉ

ኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የሁለቱ መሪዎች መገናኛ ሲንጋፖር ሆናለች

ለሳምንታት የቀጠሮው ቦታ ሲተነበይ ቆይቷል። በመጨረሻም የዶናልድ ትራምፕና የኪም ኡን መገናኛ ሲንጋፖር ሆናለች፤ ።

አብዝቶ ትዊት በማድረግ የሚታወቁት ትራምፕ በገጻቸው እንዳሰፈሩት "ሁለታችንም ለዓለም ሰላም ስንል ይቺን ቀን ልዩ ለማድረግ እንሞክራለን" ብለዋል።

ባለፈው ኅዳር ነበር ዶናልድ ትራምፕ ኪምን ለማግኘት መወሰናቸውን ይፋ በማድረግ ዓለምን ያስደነቁት።

አንድ በሥልጣን እርከን ላይ ያለ የአሜሪካ መሪ የሰሜን ኮሪያ መሪን ለማግኘት ሲፈቅድ ትራምፕ የመጀመርያው ናቸው።

ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ያልተገባ ቃላትን ሲለዋወጡ ነበር።

የመሪ በማይመስል ሁኔታም ተዘላልፈዋል።

ትራምፕ ሲንጋፖር መገናኛቸው እንደሆነች ይፋ ያደረጉት ሰሜን ኮሪያ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩትን ሦስት አሜሪካዊያንን በክብር ከተቀበሉ በኋላ ነበር።

ይህ ከመሆኑ በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዮ ወደ ፒዮንግያንግ ተጉዘው ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸው ተሰምቷል።

የሦስቱን አሜሪካዊያንን ከእስር መለቀቅ የተደራደሩትም እኚሁ ቲለርሰንን የተኩት አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው።

"አንድ ትርጉም ያለው ነገር እንደምንፈጽም እድል ያለን ይመስለኛል" ሲሉ ዓለም ከሁለቱ መሪዎች ስብሰባ አንድ ውጤት እንዲጠብቅ ተስፋን ሰጥተዋል፤ትራምፕ።

ትራምፕና ኪም የሚገናኙት የፊታችን ሰኔ 12፣ 2018 ይሆናል።

ለምን ሲንጋፖር?

ሲንጋፖር ትንሽ ነገር ግን የበለጸገች ደሴት ናት። ከዚህ ቀደም ትልልቅ ዲፕሎማሳዊ ስብሰባዎችም አስተናግዳለች።

ለምሳሌ በ2015 ባላንጣዎቹ ቻይናና ታይዋን ከ60 ዓመታት ኩርፊያ በኋላ ታሪካዊ ድርድር ያደረጉት በሲንጋፖር ነበር።

በትራምፕ ረዳቶች ዘንድ ገለልተኛና ምቹ አገር ተደርጋ ትታያለች።

ሲንጋፖር ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት አገር ናት።

ከሰሜን ኮሪያም ጋር መልካም የንግድ ግንኙነት ነበራት። ሆኖም ከባለፈው ዓመት ኀዳር ጀምሮ በሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ ግንኙነታቸው ተቋርጧል።

ያም ሆኖ ለኪምም ሆነ ለትራምፕ ገለልተኛና የተሻለች አገር ሆና ተመርጣለች።

ከዚህ ቀደም የሁለቱ አወዛጋቢ መሪዎች መገናኛ ሞንጎሊያ አልያም የሁለቱ ኮሪያዎች ከጦር ቀጠና ውጭ የተደረገው የድንበር ከተማ ይሆናል የሚል ግምት ሲሰጥ ሰንብቷል።