በኬንያ ግድብ መደርመስ 41 ሰዎች ሞቱ

ነዋሪዎቹ ቤቶቻቸው ግድቡን ጥሶ በወጣ ጎርፍ ተወስዶባቸዋል። Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ከሁለት ሺህ ነዋሪዎች በላይ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል

ከትናንት በስቲያ ረቡዕ መጠኑ ከፍ ያለ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ግድቡን ደርምሶ የወጣ ጎርፍ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ጠራርጎ ወስዷል፤ የሰዎችንም ሕይወት አጥፍቷል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ብቻ በትንሹ 41 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።

የግድቡ መደርመስ የተከሰተው ከናይሮቢ ሰሜን ምዕራብ 190 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ሶላይ በተባለች ከተማ ነው።

ከሞቿቹ መሐል በጭቃ ውስጥ ተይዘው ሕይወታቸውን ያጡ ሕጻናትና ሴቶች ይገኙበታል።

የኬንያ ቀይ መስቀል 40 ሰዎችን ከአደጋው መታደጉን ተናግሯል።

በዚሁ የግድብ መደርመስና ጎርፍ አደጋ ከሁለት ሺህ ሰዎች በላይ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በኬንያ ከባድ ዝናብ የሚያስከትለው ጎርፍ ተከትሎ ባለፉት ወራት ብቻ በርካታ ሰዎች በደራሽ መወሰዳቸው ተዘግቧል።

ይህ ከባድ ዝናብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለምግብ እርዳታ የዳረገውን ድርቅ ተከትሎ የመጣ ነው።

አስራ አንድ የሚሆኑ ሬሳዎች በጎርፍ ተወስደው በቡና እርሻ ውስጥ መገኘታቸውን ኤኤፍፒ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። ምናልባትም ሟቹቹ የግድቡን መደርመስ ተከትሎ ለማምለጥ ሲሞክሩ ደራሽ ወንዝ ይዟቸው ሳይሄድ እንዳልቀረ ግምት ተይዟል።

ይህ ፓቴል የሚባለው ግድብ በአንድ የግል እርሻ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ለመስኖና አሳ ለማስገር አገልግሎት ላይ የዋለ ነበር። ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ግድቡ ፈርሶ በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ጠራርጎ ወስዷቸዋል።

አብዛኛው የተፋሰሱ አካባቢ በደራሽ ውኃ በመወሰዱ የመብራትም ሆነ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።

አንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጎርፉ ሲጥለቀለቅ ሌላ የአካባቢው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ በጎርፉ ተወስዷል።

ተያያዥ ርዕሶች