ረመዳን፡ ጾም በሰውነታችን ውስጥ የሚያስከትለው ለውጥና የሚሰጠው ጥቅም

ምስለ-ሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሙስሊሞች ከጸሐይ መውጫ እስከ ጸሐይ መግቢያ ድረስ ይጾማሉ። ይህ ከጤና አንጻር ምን ትጽእኖ ይኖረዋል?

ታላቁ የረመዳን ጾም ወቅት እነሆ ተጀምሯል።

በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ በጉጉት የሚተበቀው ይህ ወቅት ቀኑ በጾም ምሽት ላይ ደግሞ ከቤተሰብና ከዘመድ ጋር ተሰብስቦ በአንድነት ማፍጠር የተለመደ ነው።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ዓለማችን በገጠማት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ላይ ተሰብስቦ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን መካፈልና ከተለያዩ ሰዎች ጋር መሰባሰብ እንዲቀር ይመከራል።

ስለዚህም በሐይማኖት አባቶች የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ይህንን ቅዱስ የጾም ወቅት እራሳችንንና ሌሎችን በመጠበቅ ልናሳልፈው ይገባል።

በወረርሽኙ ምክንያት ምዕመናን ቀደም ሲል ሲያከናውኗቸው የነበሩ የጋር ሥርዓቶችን ማድረግ ባይችሉም፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከቅርብ የቤተሰብ አባላቸው ጋር የተለመደውን ሥርዓት መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።

መጾም ታላቅ መንፈሳዊ ጸጋ እንደሚያስገኝ የሐይማኖት አባቶች ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ጾም ከሚያስገኘው መንፈሳዊ በረከት በተጨማሪ ለአካላዊ ጤንነት የሚሰጠው ጠቀሜታ አለው ይላሉ። ዝርዝሩን እነሆ. . .

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ረመዳንን በጾም ያሳልፋሉ። ጀንበር ወጥታ እስክትጠልቅ ድረስ።

ሰውነታችን ከጾም ጋር የሚተዋወቀው ለመጨረሻ ጊዜ ምግብ ከቀመስን ከስምንት ሰዓታት በኋላ ነው። ይህም ማለት አንጀታችን ከተመገብነው ምግብ የሚያገኛቸውን ንጥረ ነገሮች በሙሉ አሟጦ ከጨረሰ በኋላ ነው የሚሆነው።

ከዚህ በኋላ ሰውነታችን ተስፋ ይቆርጥና ፊቱን ጡንቻችንና ጉበታችን ውስጥ ወደተከማቸ ጉሉኮስ ያዞራል። የተቀረው የሰውነታችን አካል ጉልበት የሚያገኘውም ከዚህ የመጠባበቂያ 'ግምጃ ቤት' ከሚያገኘው ኃይል ይሆናል ማለት ነው።

ከጡንቻና ከጉበት የጉሉኮስ ክምችት ሲያልቅ ሰውነታችን ሌላ አማራጭ ስለማይኖረው ስብን (Fat) ማቃጠል ይጀምራል። ከዚህ በኋላ ሙቀትና ጉልበትን የሚያገኘውም ከሌላ ሳይሆን ስብን በማቃጠል ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ መልካም ነገሮች ይከሰታሉ። የሚቃጠለው ስብ በመሆኑ ክብደት መቀነስ፣ የኮሌስትሮል መጠን መውረድ ይኖራል። የስኳር መጠናችን በዚህ ወቅት ዝቅ ማለቱ አይቀርም።

ሆኖም በደማችን ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ስለሚቀንስ ድካምና መዛልን ያስከትልብናል።

ይህን ተከትሎ መጠነኛ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና መልካም ያልሆነ የአፍ ጠረን ሊከተል ይችላል። ይህ የሚሆነው በረሀብ ምክንያት ሆዳችንን ሲሞረሙረንና ያለ ምግብ መቆየቱ ለሰውነታችን እየከበደው ሲመጣ ነው።

ከ3-7ኛ ቀን፤ ሰውነታችን በፈሳሽ እጥረት የሚጎዳበት ጊዜ

ሰውነታችሁ ጾሙን እየተለማመደ ሲመጣ በውስጣችን የሚገኘው የስብ ክምችት እየተሰባበረ ራሱን ወደ የደም ስኳርነት (Blood sugar) ይለውጣል።

የምንወስደው ፈሳሽ መጠን እየቀነሰ መምጣቱ በሰውነታችን ውስጥ ያለው ፈሳሽ ወደመሟጠጥ (ዲሃይድሬሽን) ስለሚያመራ በ"ማፍጠሪያ" ሰዓትና ከዚያም በኋላ ባለው የሌሊቱ ክፍለ ጊዜ በርከት ያሉ ፈሳሾችን መውሰድ ይመከራል።

በጾም መግደፊያ ሰዓት የምትወስዱት የምግብ መጠን ጉልበት ሰጪ የሆኑ ተመጣጣኝ ምግቦችን ማግኘት ይኖርበታል።

በፕሮቲን ከበለጸጉ ምግቦች ባሻገር ጨው እና በርከት ያለ ውኃ ከሌሎች የተመጣጠኑ ምግቦች ጋር ማግኘት ለሰውነታችን መልካም ሁኔታን ይፈጥራል።

ከ8ኛ-15ኛ ቀናት

በዚህ ጊዜ ሰውነታችን ጾሙን ተላምዶታል። በዚህም የተነሳ ድካምና መዛሉ እንደመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

ዶክተር ራዚን ማህሩፍ የአኔስቴሺያና የጽኑ ሕሙማን ሕክምና አማካሪ ናቸው። በኬምብሪጅ አዴንብሩክ ሆስፒታል ውስጥ ነው የሚሠሩት። እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ጊዜ ጾሙ ለሰውነታችን ሌላም በጎ ጎን ይዞ ይመጣል።

ለምሳሌ በሌላው ጊዜ በርከታ ያለ ካሎሪ ያላቸው ምግቦችን የምንወስድ ከነበረ ሰውነታችን ሥራዎችን በአግባቡ ለመፈፀም ፈተና ውስጥ ይወድቅ ነበር። ወይም ደግሞ እክል ይገጥመዋል። በጾም ጊዜ ግን ይህ ሁኔታ ይስተካከላል።

"ምክንያቱም የካሎሪ ክምችት ስለማይበዛበት ሰውነታችን ወደ ሌሎች ሥራዎች ትኩረቱን ያደርጋል" ይላሉ ሐኪሙ። ለዚህም ነው "ጾም ኢንፌክሽን በመዋጋትና ጤናን በመመለስ አስተዋጽኦ የሚኖረው።"

ከ16ኛ- 30ኛ ያሉ ቀናት

በረመዳን ሁለተኛው ምዕራፍ (ከ15ኛው ቀን ጀምሮ) ሰውነት ሙሉ በሙሉ ጾሙን ይላመዳል። በዚህ ጊዜ እነ ደንዳኔ፣ ጉበት፣ ኩላሊት እንዲሁም ቆዳ ሁሉም ራሳቸውን በማጽዳት ሂደት (ዲቶክሲፊኬሽን) ውስጥ ነው የሚሆኑት።

ዶክተር ማህሩፍ እንደሚሉት በዚህ ወቅት ጤና ተመልሶ፣ ሰውነታችን የቀድሞውን ጉልበቱን የሚያገኝበትና የማስታወስ አቅምና ትኩረት የማድረግ ብቃት ወደ ቀድሞው ሁኔታ የሚመለስበት ጊዜ ነው።

በዚህ ጊዜ ሰውነታችን ጉልበት ለማግኘት ወደ ፕሮቲን መሄድ አይኖርበትም። ይህ የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ረሀብ ሲሰማንና ሰውነታችን ከጡንቻዎቻችን እየቀሰመ የሚወስደውን ምግብ ማደን ሲጀምር ነው። በዚህ መንገድ የሚቀጥለው ግን ለቀናትና ለሳምንታት በተከታታይ ስንጾም ነው።

የረመዳን ጾም የሚጸናው የየዕለቱ ጀምበር ወጥታ እስክትጠልቅ ብቻ ስለሆነ ሰውነታችን ጉልበት ከምግብ እንዲያገኝ የ"ኢፍጣር" ሰዓት ዕድል ይሰጠዋል። ፈሳሽም እንደልብ ያገኛል።

ይህ ጡንቻዎቻችን ውስጥ ያለን ክምችት ለመጠባበቂያነት ያቆይልናል። የተወሰነ ኪሎ እንድንቀንስም ይረዳናል። ይህም ለሰውነት መልካም ነገር ነው።

ጾም ጤናን ይጎዳል?

የካምብሪጁ አዲንብሩክ ሆስፒታል ሐኪም ዶክተር ማሕሩፍ ምላሻቸው "እንደሁኔታው" የሚል ነው። እንደርሳቸው አመለካከት በርከት ያሉ ሁኔታዎች ጾምን ለሰውነታችን ጎጂም ጠቃሚም ሊያደርጉት ይችላሉ።

ጾም ለሰውነታችን መልካም የሚሆንበት አንዱ ምክንያት መቼ ምን መብላት እንዳለብን ትኩረት እንድናደርግ ስለሚያስችለን ነው። ሁለተኛው ክብደታችንን መቆጣጠርና፣ የካሎሪ መጠን መወሰን ስለሚያስችል ነው።

ለወር ያህል መጾም እምብዛምም የሚያመጣው የጤና እክል ባይኖርም ከዚያ በኋላ ግን ለተከታታይ ጊዜ ያለማቋረጥ መጾም ግን አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ሐኪሙ ሳይጠቁሙ አያልፉም።

እንደ ሐኪሙ ማብራሪያ ያለማቋረጥ መጾም በቋሚነት ኪሎ ለመቀነስ አይረዳም። ምክንያቱም ከሆነ ጊዜ በኋላ ሰውነታችን ስብን ወደ ጉልበት መቀየር ያቆምል። ከዚያ ይልቅ ፊቱን ወደ ጡንቻዎቻችን ነው የሚያዞረው።

ይህ ደግሞ ጤናማ አይደለም። ምክንያቱም ሰውነታችን ከሆነ ወቅት በኋላ "በመራብ ስሜት" ላይ ስለሚቆይ ነው።

ሐኪሙ እንደሚሉት ከረመዳን ውጭ መጾም ቢያስፈልግ እንኳ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ እያፈራረቁ መጾም በመደዳ ለተከታታይ ቀናት ከመጾም እጅግ የተሻለ ጤናማ ተግባር ነው።

"ረመዳን በአግባቡ ከተጾመና በቂ ፈሳሽ በቀን ውስጥ ማግኘት ከተቻለ፣ ጠቃሚ የጡንቻ ክምችቶች ሳይቃጠል ኪሎ መቀነስ ስለሚያስችል የጤና በረከትም ያስገኛል" ይላሉ እኚሁ ሐኪም።