ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ልታደርገው የነበረውን ጉባኤ ልሰርዝ እችላለሁ ስትል አስፈራራች

ኪም ጆንግ ኡን እና ዶናልድ ትራምፕ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ሁለቱ መሪዎች ከአንድ ወረ ገደማ በኋላ በሲንጋፖር ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል

አሜሪካ በብቸኝነት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ስራዬን እንዳቋርጥ የምትጫነኝ ከሆነ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የሚደረገው ጉባዔ ላይ ላልሳተፍ እችላለው ስትል ሰሜን ኮሪያ አስፈራራች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከአንድ ወር በኋላ ፊት ለፊት ይገናኛሉ ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

ይሁን እንጂ የሰሜን ኮሪያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቁጣ በተሞላበት ንግግር የአሜሪካንን 'ግድ የለሽነት የተሞላበት መግለጫ' ኮንነዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ንግግር በአሜሪካው ብሄራዊ የፀጥታ አማካሪ ጆን ቦልተን ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ጆን ቦልተን ሰሜን ኮሪያ ሊቢያ ስትከተለው የነበረውን የጦር መሳሪያ ቅነሳ አሰራር ሂደትን ልትከተል ትችላለች በሚል አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።

"ይህ አደገኛ የሆነ ሃሳብ ሲሆን አገራችንን እንደ ሊቢያና ኢራቅ የመከላከያ አቅሟን በማዳከም ወደ ቀውስ ውስጥ የሚከትና እንድትወድም የሚያደርግ ነው። በመሆኑም በእርሱ ላይ ያለንን የጥላቻ ስሜት ለመደበቅ አንፈልግም" ሲሉ አክለዋል።

ይህ ንግግር በተለያየ የስልጣን ተዋረድ ላይ ያሉ የሰሜን ኮሪያ ተፅእኖ ፈጣሪ ባለስልጣናትን ይወክላል ተብሏል።

ከአንድ ወር በኋላ በሲንጋፖር ለሚካሄደው የሁለቱ አገራት መሪዎች ጉባዔ አሁንም ዝግጅቱ እየተደረገ ነው።

ኪም እና ትራምፕ ፊት ለፊት ለመገናኘት የተስማሙት ሰሜን ኮሪያ የኮሪያን ሰርጥ ከኒዩክሌር ነፃ አደርጋለሁ በማለት በመስማማቷ ዋና መሰረት በማድረግ ነው።

ኪም ጉባዔው በኮሪያዋ ሰርጥ ያለውን ሁኔታ የሚያረግብ እንዲሁም መጭውን ጊዜ ጥሩ ለማድረግ ትልቅ እርምጃ እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

''በጉባኤው መዳረሻ ላይ ያልተጠበቀና ትክክል ያልሆነው የአሜሪካ ድርጊት ይህንን መግለጫ እንድንሰጥ አስገድዶናል። ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሳቸው በፊት የነበሩ መሪዎችን አይነት እስርምጃ ከተከተሉ ከቀድሞዎቹ በባሰ በጣም አሳዛኝና ስኬታማ ያልሆነ መሪ ሆኖ ይመዘገባል።'' ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በአገራቱ መካከል ከጦር ነፃ የሆነ ቀጠና ለመፍጠርና በስምምነቱ ላይ ተጨማሪ ምክክር ለማድረግ ባለፈው ወር ታሪካዊ ጉባዔ አድርገው ነበር።