የኢትዮጵያ ተረት ገፀ-ባህሪን በአኒሜሽን

ፌበን

"ተረት ተረት" ሲባል "የላም በረት" ለማለት ከሚፈጥኑ ልጆች አንዷ ነበረች። ከልጅነት ትውስታዎቿ ተረት ትሰማ የነበረበተ ጊዜያት ዋነኞቹ ነበሩ ።

አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የ26 ዓመቷ ፌበን ኤልያስ በህንጻ ኮሌጅ ኧርባን ዲዛይን ስትማር ከምህንድስና በበለጠ የሶስት አውታር ንድፍና ግራፊክስ ዲዛይን ይስባት ነበር።

የእንጀራ ገመዷን የዘረጋችውም በዚህ ሙያ ነው። በአርማ አድቨርታይዚን ውስጥ ንድፍና አኒሜሽን ትሰራለች።

"ጎረቤቴ ሚጢጢ የአኒሜሽን መነሻዬ"

ያሳደጓት አያቶቿ ናቸው። ሚጢጢ የምትባል የጎረቤት ታዳጊ ነበረች።

ሚጢጢ ለየት ያለ ባህሪ ስለነበራት የሰፈሩ ልጆች ባጠቃላይ ይወዷታል። ፌበን ደግሞ ጎረቤቷን ከመውደድ ባለፈ የህጻናት አኒሜሽን ገጸ ባህሪ መነሻ አደረገቻት።

"ጠያቂነቷ፣ አልበገር ባይነቷ፣ በራስ መተማመኗ፥ ለማወቅ ካላት ጉጉት ጋር ተደማምሮ ተወዳጅ አድርጓታል" ትላለች ጎረቤቷን ስትገልጽ። ልጆች በጣም ስለሚወዷት የሷን የጸጉር አሰራርና አኳኋንም ይከተሉ ነበር።

ፌበን ጎረቤቷን ተመርኩዛ 'ድንቢጥ' የተባለች ገጸ ባህሪ ለመፍጠር የወሰነችው በልጆች ዘንድ ተወዳጅ እንደምትሆን በማመን ነው።

ከዪኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ ለስድስት ወር የሶስት አውታር ንድፍ ስልጠና በድረ ገፅ ተከታታለች። የድንቢጥን ፊልም በቤቷ ኮምፒውተር ትሰራም ጀመር።

'ድንቢጥና አያቷ'

"አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ልጆች ከገጸ ባህሪዋ ጋር እንዲተሳሰሩ ለማድረግ ሞክሬያለሁ" ትላለች።

ድንቢጥን የምትገልፃት "የልጅነት ተሞክሮዎቼን አንድ ላይ አዋህጄ የፈጠርኳት ገፀ ባህሪ ዘወትር አዳዲስ ነገር ለመሞከር ትነሳሳለች" በማለት ነው።

ፊልሙ ላይ ድብንቢጥ የምትኖረው ከአያቷ ጋር ሲሆን፣ ጸጉሯ እንደ ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ልጆች ጥቁርና ከርዳዳ ነው። የምትለብሰውም ጥበብ ቀሚስ ነው።

"ድንቢጥና የፕሪሙ ፍሬ" ከአኒሜሽን ክፍሎቹ አንዱ ነው። በድንቢጥ ቤት አቅራቢያ የፕሪም ዛፍ አለ። የፕሪሙ ፍሬ ሳይበስል እንዳትበላ ቢነገራትም አእምሮዋ ከመጠየቅ የማይቦዝነው ድንቢጥ "ያልበሰለ ፕሪም ጣዕም ምን ይሆን?" ስትል ትጠይቃለች። ጠይቃም አትቀር ትቀምሰዋለች።

"ታሪኩ ጠያቂ መሆንና በራስ መንገድ መሄድን ለልጆች ያስተምራል።" ትላለች ፌበን።

ፌበን የድንቢጥን ታሪክ ዲጂታል ላብ አፍሪካ በተባለ ውድድር ያቀረበችው ከወራት በፊት ነበር።

በውድድሩ ከአፍሪካ ሀገሮች የተውጣጡ 750 ሰዎች ተሳትፈው ነበር። ከነዚህ መሀከል አስሩ በሰምስት ዘርፍ አሸንፈዋል። በአኒሜሽን ዘርፍ ያሸነፈችው ፌበን የ3,000 ዪሮ ተሸላሚ ሆናለች።

በቀጣይ የድንቢጥ ታሪክ ተከታታይ ፊልም ከዛም የህጻናት መጽሐፍ ይሆናል።

ኢትጵያዊት ገጸ-ባህሪ

ሲንድሬላ በዋልት ዲዝኒ ከተፈጠሩ ልቦለዳዊ ገጸ ባህሪዎች አንዷ ነች። ከአሜሪካ አልፋ በመላው አለም የብዙ ህጻናትን ልብ ማርካለች።

የሲንድሬላ አይነት አለባበስና ባህሪ 'ተወዳጅና ተመራጭ' መሆኑን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን ይሰብካሉ። ሁሉም ሕጻናት የየሀገራቸው እውነታ እንዳላቸው የተዘነጋም ይመስላል።

"የኛን ታሪክ የሚያሳዪ የልጆች ፊልሞች እምብዛም አይደሉም። ይህ የፈጠረው ክፍተት የአፍሪካ ህጻናት ወደ አውሮፓውያን ፊልሞች እንዲያማትሩ አስገድዷል" ስትል ፌበን ትናገራለች።

"ሰውነታቸውን ታጥበው ሲጨርሱ ጸጉሬ ለምን እንደ ሲንድላ አልተኛም የሚሉ ልጆች ገጥመውኛል" ትላለች። የዚህ አመለካከት ለመለወጥ ያስችል ዘንድ ድንቢጥ ከርዳዳ ጸጉርና ወፍራም ከንፈር አላት።

ፌበን "ልጆች የፌበንን ጸባይ እና መልክ ከራሳቸው ጋር አስተሳስረው ደስ እንድትላቸው እፈልጋለሁ። በአስተዳደጓ፣ በባህሪዋና በመልኳ እነሱን የምትመስል ገጸ ባህሪ እያዪ እንዲያድጉ እፈልጋለሁ" ስትል ትገልጻለች።

ከአፋዊ ታሪክ ነገራ ወደ ዲጂታል አኒሜሽን

ታሪክ ነገራ ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም። ለዘመናት ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ተሸጋግሯል።

በዲጂታል ዘመን አፋዊ ታሪክ ነገራ ወደ አኒሜሽንና ካርቱን እየተለወጠ ነው። ብዙ ባለሙያዎች የህጻናት አኒሜሽንና ካርቱን ይሰራሉ።

ፌበን ፊልሞቹ በጥራት ረገድ ብዙ ይቀራቸዋል የሚል አቋም ያላት "ይዘታቸው ጥሩ ነው። አሰራሩ ግን ወደኋላ የቀረ ነው። አለም ከሚሰራው አንጻር መወዳደር አልቻልንም" ትላለች።

ትምህርት ቤት አለመኖሩ የእውቀት ክፍተቱን ፈጥሯል። ብቃት ያላቸው ስቱድዮችም ብዙ አይደሉም።

የህጻናት ታሪክ በህጻንት ስነ ልቦናዊ እድገት

ተመራማሪዎች በህጻናት እድገት ሚና አላቸው ከሚሏቸው ልቦለዳዊ ታሪኮች ይገኙበታል። ፌበንም የህጻንት እድገትና የሚነገራቸው ታሪክ ትስስር ጠንካራነቱን ታምናለች።

"ልጆች ከራሳቸው ጋር ማስተሳሰር የሚችሉትና የሚወዱትን ገጸ ባህሪ የማስመሰል ባህሪ ኣላቸው" ትላለች

ልጆች የድንቢጥን ጠንካራ ጎኖች እንዲወስዱ የምትፈልገውም ለዚሁ ነው።

የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መብዛት የአኒሜሽን ፊልሞችን ተደራሽነት ያሰፋዋል ብላም ታምናለች።

"ፊልሙን ቤተሰብና ልጆች በቴሌቭዥን በጋራ እንዲያዪት እፈልጋለሁ" ትላለች።

ተያያዥ ርዕሶች