ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ተጨባጭ ያልሆነ መረጃ ላይ ዘመቻ ጀመሩ

Uhuru Kenyatta Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ አዲሱ ህግ የሳይበር ጥቃት የሚያደርሱ ወንጀለኞችን በህግ ለመጠየቅ ያስችላል ብለዋል።

ለምስራቅ አፍሪካ አዲስ የሆነውና በኬንያ የወጣው አዋጅ ተጨባጭ ያልሆነ መረጃ የሚያሰራጩ ሰዎች ላይ እስራትን ያስከትላል።

አዋጁ 50000 የአሜሪካ ዶላር እና እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ያስከትላል።

አዋጁ በኮምፒውተርና በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር በሚል የወጣ ቢሆንም በኬንያ፣ በኡጋንዳ እና በታንዛኒያ የወጡት ህጎች ነጻ ሚዲያዎችን ለመቆጣጠር የተዘረጉ አዲስ ዘዴዎች መሆናቸውን ተቺዎች ይሞግታሉ።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ያፀደቁት አዋጅ ሃሳብን በነፃ የመግለፅንና የፕሬስ ነፃነትን ይፃረራል ሲሉ ህጉን ተቃውመዋል።

አዋጁ የሚድያ ነፃነትን ከመጋፋቱም በላይ ኬንያ ሚዲያን የተመለከተ ህግ እያላት ለምን ተጨማሪ አዋጅ ማውጣት አስፈለጋት ሲሉ ጠይቀዋል።

ፕሬዚደንቱ በበኩላቸው አዋጁ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል፣ የህፃናት የወሲብ ፊልሞችን፣ የኮምፒውተር ጥቃትንና መረጃ ምንተፋን ለመቆጣጠር ይውላል ብለዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የኬንያ ሚዲያ አዲሱን ህግ ስራቸውን እንደሚቆጣጠር አዲስ ዘዴ አይተውታል

በበርኒንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዲሞክራሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኒክ ቺዝማን ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የፀደቀው አዋጅ በሌላ አጀንዳ ምክንያት የመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"ከፍተኛ የሆነ የተጋረጠ አደጋ አለ። ከዚህ በፊትም ከፀረ ሽብር ህጉ ጋር የተያያዘ ህግ ወጥቶ ነበር። መንግሥታት የራሳቸውን አቅም ለማጠናከር ያወጡት አዋጅ ነው" ብለዋል።

ሌሎችም በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም ወደወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ይወስደናል። መንግሥትን የሚያጣጥል እና የመንግሥት ባለስልጣናት የማይፈልጉትን ፅሁፍ የፃፉና በገፆቻቸው ላይ አስተያየት የሰጡ ጦማሪያንን ለእስር የዳረገ ነው። ይህም አዋጅ ከዚያ ተለይቶ አይታይም" ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዚደንት ጆን ማጉፋሊ አነጋጋሪ ህግ አውጥተዋል

በቅርቡ በጎረቤት አገር ታንዛኒያም የወጣው ህግ ከዚህ የተለየ አይደለም። ህጉ ጦማሪያን ፅሁፋቸውን በኢንተርኔት አማካኝነት ሲያቀርቡ 920 የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው።

"ምንም እንኳን ሃሳብን በነፃ ከመግለፅ መብት ጋር ይፃረራል የሚሉ ትችቶች ቢሰነዘሩም፤ ህጉን ለማውጣት የተፈለገበት ምክንያትም ምስራቅ አፍሪካን ተጨባጭ ካልሆነ የመረጃ ስርጭት ለመጠበቅ ነው" ሲል የአገሪቷ መንግሥት ገልጿል።

ተጨባጭ ያልሆነ መረጃ ስርጭት በሽታ ነው ሲሉ የገለፁት ፕሬዜደንት ማጉፋሊ ዓላማው መረጃዎችን መርጦ ማስተላለፍ ነው ብለዋል።

አዲሱ ህግ ጦማሪያን፣ ኢንተርኔት በመጠቀም መልዕክት የሚያስተላልፉ ግለሰቦች እንዲመዘገቡና ለሶስት ዓመት ፍቃድ 480 ዶላር እንዲከፍሉ በተጨማሪም በዓመት 440 የአሜሪካ ዶላር ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚያዝ ነው።

ህጉን የተላለፈም 2000 የአሜሪካ ዶላር እና ከአንድ ዓመት ባላነሰ እስር እንዲቀጣ ይደነግጋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በኬንያ የሚገኙ አቀንቃኞች ሚዲያዎች መዘጋትን ባለፈው የካቲት ሲቃወሙ

የታንዛኒያን ጦማሪያን ኔትወርክ ህጉ አባላቶቻቸውን እንዳይፅፉ ወይም የሚፅፉትንም እንዲያቋርጡ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ከማለት ባለፈ ተቃዋሚ የሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎችና ግለሰቦችን ለመቅጣት የተመቻቸ ነው ሲሉ ፕሬዚደንቱን ሞግተዋል።

በሌላኛዋ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የቀረጥ የሚጥል ረቂቅ ህግ የወጣ ቢሆንም የገንዘብ ሚኒስትሩ "እንዲህ ዓይነት የቀረጥ ህግ እንዴት ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል?" ሲሉ ባቀረቡት ጥያቄ ምክንያት በጅማሮ ላይ ይገኛል።

ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቭኒ ከማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰበሰበው የቀረጥ ገቢ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋፅኦ ያበረክታል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚለቀቁ የሃሰት መረጃዎችን መቆጣጠር አለብን ብለዋል

በቅርቡ ከሚዲያ ባለቤቶችና ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ እባካችሁ እየመረጣችሁ አስተላልፉ፤ ውሸት አታሰራጩ ሲሉ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች