በኮንጎ የኢቦላ ቫይረስ እየተዛመተ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

Health workers outside the isolation ward at Bikoro hospital, Democratic Republic of Congo May 12, 2018 Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በድሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ የተጠረጠሩ ሰዎች ተለይቶ በተዘጋጀላቸው ሆስፒታል ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ኢቦላ በፍጥነት የመዛመት ጉዳይ አሳስቦት አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ።

ውይይቱ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል አለም አቀፋዊ ትኩረት ለማግኘትና የአስቸኳይ ጥሪ ለማስተላለፍ ወሳኝ ነው ተብሏል።

ኢቦላ አሁንም ቀድሞ ካገረሸበት አካባቢ ምባንዳካ ወደ ተባለ ትንሽ የገጠር አካባቢም እንደተዛመተ ታውቋል። አንድ ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች የሚኖሩባት ከተማዋ ኮንጎ ወንዝን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመጓጓዝ በመጠቀማቸው ቫይረሱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።

ዋና ከተማዋን ኪንሻሳን እና በዙሪያዋ ያሉ ሌሎች ከተሞችንም አስግቷል።

በቅርቡ እንደገና ባገረሸው ኢቦላ በትንሹ 44 የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ 23 የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ እንደሞቱ ተረጋግጧል።

ኢቦላ የሰውነት መድማትን የሚያስከትል ኢንፌክሽን ሲሆን ከሰውነት በሚወጡ አነስተኛ መጠን ባለቸው ፈሳሸ ሳይቀር በንክኪ ምክንያት በመተላለፉ እንዲሁም ያልተለመዱ ምልክቶች ስላሉት በፍጥነት እንዲዛመት ምክንያት ሆኗል።

ኢቦላ ለምን አገረሸ?

የአለም ጤና ድርጅት ባላስልጣን ፒተር ሳላማ በሽታው በአጭር ጊዜ ወደ ምባንዳካ መዛመቱ ወደሌሎች አገራትም የመዛመት ዕድሉን ያሰፋዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አጠቃላይ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ምክትል ዳይሬክተር እንዳሉት ኢቦላው በኮንጎ ወንዝ አቅራቢያ ከምትገኘው ምባንዳካስ ወደ ኮንጎ ብራዛቪል እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሊዛመት ይችላል ብለዋል።

በተለያየ አቅጣጫ መመልከታችን በምባንዳካ የታየውን የመሰራጨት እድል ለማቆም አስቸኳይ እርምጃ ለመውስድ ያስችላል ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

እአአ ከ2014-2016 ምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው ኢቦላ ወደ ጊኒ፣ ሴራሊዮንና እና ላይቤሪያ በመዛመቱ ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

ኢቦላን ለመቆጣጠር ምን ተሰራ?

የዓለም ጤና ድርጅት 44 የኢቦላ ኬዞችን እንዳገኙና ከእነዚያ መካከል 20 የሚሆኑት በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩና ቀሪዎቹ 21 የሚሆኑት ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ጥርጣሬ እንዳላቸው አስታውቋል።

ኬዞቹም በምባንዳካ የኮንጎ ኢኳተር ክፍል እንደተመዘገቡ ተነግሯል።

ምክትል ዳሬክተሩ እንደተናገሩት በከተማዋ የተለየ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ገልፀው በሽታው በቢኮሮ ከተማ በኢቦላ የሞቱ ሰዎች የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ከተማዋ በሄዱ ሰዎች አማካኝነት ሳይዛመት እንዳልቀረ ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ረቡዕ 4000 የሚሆን የሙከራ ክትባት ኪንሻሳ የደረሰ ሲሆን ተጨማሪ ክትባት በቅርቡ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ክትባቱ በምባንዳካ ከተማ ለሚኖሩና ቫይረስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ላላቸው ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣል ሲሉ ምክትል ዳሬክተሩ ተናግረዋል።

ፈቃድ ባያገኝም ከዚህ ቀደም በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላ ተከስቶ በነበረ ጊዜ በተወሰነ መልኩ ሙከራ ተደርጎ አዋጭ እንደነበር የተናገሩት ዳሬክተሩ ክትባቱ -60እና -80 ሴልሽየስ የሙቀት መጠን መቀመጥ የሚኖርበት ቢሆንም በኮንጎ ያለው የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማመኝ ባለመሆኑ የክትባቶቹን ቁጥር ለመጨመር አዳጋች አድርጎታል ይላሉ።

ስርጭቱን በአፋጣኝ ለመቆጣጠር የዓለም ጤና ድርጅት ሰራተኞች ከቫይረሱ ጋር ንክክኪ አላቸው የተባሉ 430 ሰዎችን የለዩ ሲሆን ሌሎች ከኢቦላ ታማሚዎች ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ 4000 ሰዎችን የመለየት ስራ እየሰሩ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ናቸው።

ኢቦላ ደግሞ ደጋግሞ ለምን አገረሸ

ከ2014-2016 በድሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወረርሽኑ ለሶስተኛ ጊዜ አገርሽቷል። ኢቦላ ፍራፍሬ በሚመገቡ የሌሊት ወፎችና ከዱር እንስሳቶች ጋር ግንኑነት ባላቸው ሰዎች አማካኝነት በመተላለፉ ድንበር ሳይከልልው ይዛመታል።

በሽታው ከያዛቸው እንስሳት በደም እና በአካል ንክኪ እንዲሁም በሌላ የሰውነት ፈሳሾች ይተላለፋል። ዝንጀሮዎች፣ ቺምፓንዚዎች፣ አጋዘኖች እና ጎሪላዎች በሽታውን ከሚያስተላልፉ እንስሳት ይጠቀሳሉ።

በሽታውን የሚያዛምቱ ሁሉንም እንስሳትን ማጥፋት ስለማይቻልና ሰዎች ከእንስሳቶቹ ጋር ግንኙነት እስካላቸው ድረስ ኢቦላ መልሶ መላልሶ ሊያገረሽ ይችላል።