ጥቃት የተፈጸመበት ታዳጊ ባህር ዳር ደርሷል

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ Image copyright OCHA

ባሳለፍነው ሰኞ ግንቦት 6 2010 ዓ.ም በመተከል ዞን፤ ድባጤ ወረዳ እድሜው አስራ ሦስት እንደሆነ በሚገመት ሕፃን ልጅ ላይ በስለት በተፈጸመ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ጥቃቱን በተመለከተ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ብዙ መረጃ እየወጣ ሲሆን፤ ጉዳዩን ለመማረጋገጥ የታዳጊው የቅርብ ቤተሰብ የሆኑት አቶ አያሌው አበረን ቢቢሲ አነጋግሯቸው ነበር።

እንደ አቶ አያሌው ምስክርነት ከሆን ታዳጊው ጥቃቱ በተፈጸመ ወቅት የመራቢያ አካሉ የተቆረጠ ሲሆን፤ ፊቱም ላይም በካራ ከፍተኛ መቆራረጥ ተፈፅሞበታል። ሦስት የፊት ጥርሶቹም ረግፈዋል።

ታዳጊው በደረሰበት ጉዳት ራሱን ስቶ የቆየ ሲሆን ከሁለት ቀናት በፊት ግን መናገር እንደጀመረ እና ጥቃቱን ያደረሰበት ግለሰብ በወቅቱ ጫት እየቃመ እንደነበረ ታዳጊው ነግሮናል ሲሉ አቶ አያሌው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አያሌው ጨምረው እንደተናገሩት፤ ግለሰቡ ሲያጫውተው እንደቆየና ድንገት ማጅራቱን ሲመታው መሬት ላይ በመውደቅ ራሱን ስቷል።

ታዳጊው ሲያግዳቸው የነበሩት ከብቶች ከምሽቱ 12 ሰዓት አካባቢ ብቻቸውን ወደ ቤት ሲመለሱ ልጁ 'ያለ ወትሮው ከብቶቹን እንዴት ብቻቸውን ላከ' ብለው የቤተሰቡ አባላት ፍለጋ መውጣታቸውን ይናገራሉ አቶ አያሌው።

ፍለጋ የወጣውም ቤተሰብ በአካባቢው የታዳጊውን ስም በመጥራት ሲፈልጉት ቆይተው በመጨረሻም ጥሪውን የሰማው ታዳጊ ድምጹን በማሰማቱ ከቦታው ሲደርሱ ወድቆ እንዳገኙትና ተረባርበው ወደ ህክምና ቦታ እንደወሰዱት አቶ አያሌው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁን ታዳጊው በሚገኝበት ፓዌ ሆስፒታል ከደረሰበት ቀን ጀምሮ በነጻ ህክምና እየተደረገለት መሆኑን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ በየነ ገልጸውልናል።

ታዳጊው ለተሻለ ህክምና ወደ ባህር ዳር መላክ የነበረበት ቢሆንም ወላጆቹ የትራንስፖርት እና ተያያዥ ወጪ መሸፈን ሳይችሉ በመቅረታቸው በፓዌ ሆሰፒታል ውስጥ ለቀናት እንዲቆይ ተደርጎ ነበር፤ ሲሉ በሆስፒታሉ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ግርማ ይናገራሉ።

ትናንት ማምሻውን ግን የሆስፒታሉ ሰራተኞች ገንዘብ በማሰባሰብ ታዳጊውን ወደ ባህር ዳር የላኩት ሲሆን፤ ዛሬ ጠዋት ከቤተሰብ አባላት እንደሰማነው በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ይገኛል።

''በሆስፒታሉ በቆሁባቸው 2 ዓመታት እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሞኝ አያውቅም'' ያሉት ዶክተር ግርማ፤ የተቻለንን ህክምና አድርገንለታል ብለዋል።

ለተሻለ ህክምና ግን ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ሪፈር ስለተባለ ዛሬ ወደ ባህር ዳር ሆስፒታል መላኩንና ከባህ ርዳር ደግሞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ ጨምረው ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ደግሞ ስለ ታዳጊው በማህበራዊ ሚዲያ ከሰሙ በኋላ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ እንደቆዩ ይናገራሉ።

ዶክተር ደሳለኝ ታዳጊው ባህር ዳር ከደረሰ በኋላ ሄደው የጎበኙት ሲሆን ''ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ይገኛል'' ሲሉ የታዳጊውን ሁኔታ ገልፀዋል።

ከዶክተር ደሳለኝ እና ከሌሎች ምንጮቻችን እንደሰማነው ከሆነ አቶ በላይነህ ክንዴን ጨምሮ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የታዳጊውን የህክምና ወጪ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች