የኢቦላ መከላከያ ክትባት በኮንጎ ሊሰጥ ነው

ክትባት ለኢቦላ በሽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሽታው ምዕራብ አፍሪካን ባጠቃበት ( ከ2014-16 እ.እ.ኤ) በተደረገ ውስን ሙከራ ወቅት ነበር የክትባቱ ውጤታማነት የተረጋገጠው።

የኢቦላ ወረርሽኝ በትንሹ 26 ሰዎች ሳይገድል እንዳልቀረ በተሰጋበት በአሁኑ ሰዓት የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ከሚውስዱት መካከል የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ለመሆኑ የኢቦላ በሽታ ምንድን ነው?

ገዳዩ ኢቦላ ውስጣዊ ደም መፍሰስን የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ነው።

በሽታው የሰውነት ፈሳሽና የአካል ንክኪን ምክንያት አድርጎ በፍጥነት ይሰራጫል፤ ጉንፋን መሳይ ቀዳሚ ምልክቶቹ አንዳንዴ ላይጤኑ ይችላሉ።

ከ2014-16 እ.ኤ.አ ተከስቶ በነበረው የመጀመሪያው የበሽታው ወረርሽኝ ምዕራፍ ብቻ ከ11300 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የአሁኑ ወረርሽኝ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

ከዚህ ወር የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ በተከሰተው ወረርሽኝ፤ ሦስት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 45 ያህል ሰዎች ተጠቂዎች እንደሆኑ ተዘግቧል።

ቫይረሱ ከገጠራማ ቦታዎች ተነስቶ በሰሜን ምዕራብ ኮንጎ ወደ ምትገኘው የኮንጎ ወንዝ ዳር የመጓጓዣ ማዕከል ‹ምባንዳካ› ከተማ ተዛምቷል። በዚች ከተማ ቢያንስ አራት ተጠቂዎች እንደተገኙ ታምኗል። ይህም በምላሹ ወረርሽኙ ወደ መዲናዋ ኪንሻሳና አጎራባች ሀገራት ይዛመታል የሚል ፍርሃትን ፈጥሯል።

ዓለማቀፉ የጤና ድርጅት ግን ''ወረርሸኙ በቁጥጥር ስር ይውላል'' የሚል ጠንካራ ዕምነት እንዳለው አሳውቋል።

አርብ ዕለት በነበረ ድንገተኛ ስብሰባ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎች ''ዓለም አቀፍ የህዝብ ጤና ድንገተኛ አገልግሎት ሁኔታዎች እስከ አሁን ድረስ አልተሟሉም'' ብለዋል።

በጥቅም ላይ ስለዋለው መድሃኒት ጥቂት መረጃዎች

'መርሰክ' በተሰኘው መድሃኒት አምራች ድርጅት የቀረበው መድሃኒት እስከ አሁን ድረስ ፈቃድ ባያገኝም ወረርሽኙ ምዕራብ አፍሪቃን ባጠቃበት ወቅት በተወሰዱ ውስን ሙከራዎች ውጤታማነቱ ታይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማይክል ያዎ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ክትባቱ በጊኒ በተሞከረ ጊዜ መድሃኒቱን የወሰዱት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በሽታው ሳይዛቸው ቀርቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት 400ሺ ያክል ጥቅል መድሃኒት ወደ ኮንጎ ልኳል። ሌላ ዙር የመድሃኒት ጥቅል እንደሚያስከተልም አስታውቋል።

የጤና አገልግሎት ሰጪዎች እና የቀብር ሥነ-ስርዓት ፈጻሚ ሰራተኞች የመጀመሪያ ዙር ተከታቢዎች ይሆናሉ። ከእነርሱ ቀጥሎ ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሆኑ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር 'ንክኪ ይኖራቸዋል' ተብሎ ለታመነ ሰዎች ይዳረሳል።

የክትባት ዘመቻው ተግዳሮቶች

የክትባት ዘመቻው የመጀመሪያ እንቀፋት በሀገሪቱ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ነው። መድሃኒቶቹ ከ-60 እስከ -80 ዲግሪ ሴንትግሬድ በሆነ ቅዝቃዜ ውስጥ መቀመጥ ያስፈልጋቸዋል።

የመጀመሪያው የክትባት ጥቅል በምባንዳካ ከተማ ደርሷል፤ ሆኖም የበሽታው ስርጭት ወደ ተነገረባቸው ወጣ ያሉ ስፍራዎች ለመድረስ ጥቅጥቅ ባለው ጫካ ውስጥ መጓጓዝ ይጠበቅባቸዋል።

ሌላኛው አሳሳቢ ጉዳይ ክትባቱ እስከ አሁን ድረስ ዕወቅና ያልተሰጠው ከመሆኑ ጋር ይያዛል። መድሃኒቱ ለግልጋሎት የሚውለው ሁሉም ታማሚዎች መልካም ፈቃደኝነታቸውን በፊርማ ካረጋገጡ በኋላ ነው። በዚህም ምክንያት በጤና ባለሙያዎች እና በአካባቢው ማህበረሰብ መካካል መግባባትን ለመፍጠር አስተርጓሚዎች ያስፈልጋሉ።