ኢራን አሜሪካ ማዕቀብ እጥላለሁ ማለቷን አወገዘች

Iranians burn US and Israeli flags in Tehran, Iran, 18 May 2018

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ አሜሪካ በታሪኳ ከፍተኛ የሆነውን ማዕቀብ እጥላለሁ ማለቷን ነቅፈዋል።

በአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚያሳዩት አሜሪካ በተኮላሸው ፖለቲካዋ እስረኛ እንደሆነችና የሚመጣው መዘዝም ተቋዳሽ እንደምትሆን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ የሆኑት ፌደሪካ ሞገሪኒ በበኩላቸው አሜሪካን ተችተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2015 የተፈፀመውን የኒውክሌር ስምምነት መሰረዝ ለመካከለኛ ምስራቅ ያለውን ፋይዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማሳየት እንዳልቻሉም ገልፀዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ወር መጀመሪያ ስምምነቱን ለመተው መወሰናችውን ተከትሎ " በስምምነቱ ላይ ሌላ ምርጫ የለም በመሆኑም ኢራን ሃላፊነቷን የምትወጣ ከሆነ የአውሮፓ ህብረት በስምምነቱ ሊቀጥል ይችላል" ብለዋል።

ከኢራን የኒውክሌር ስምምነት በኋላ አንዳንድ በአውሮፓ የሚገኙ ትልልቅ ድርጅቶች በኢራን መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ የቸኮሉ ቢሆንም፤ አሜሪካ ስምምነቱን መሰረዟን ተከትሎ ኢራን ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ አሊያም ከአሜሪካ ጋር ንግድ ለመጀመር ምርጫ ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምን ተናገሩ?

አሜሪካ አዲስ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል የገለፁ ሲሆን አዲሱ አርምጃ ከዚህ ቀደም ያልተደረገ የገንዘብ ጫናን ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

ከኢራን ጋር አዲስ ስምምነትም የሚደረስ ከሆነ ወታደራዊ ሃይሏን ከሶሪያ እንድታስወጣና የየመን አማፂያንን ድጋፍ ማቆም እንዳለባት ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

የቀደመው ማዕቀብ ከኢራን ጋር የሚኖረውን የንግድ ትስስር የሚከለክል ነበር።

ማይክ ፖምፔዮ አዲሱ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል በዝርዝር አልተናገሩም ።

ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት በኢራን ማዕከላዊ ባንክ ላይ ማዕቀብ የተጣለ ሲሆን፤ ይህም የእርምጃው መጀመሪያ ነው ብለዋል።

ኢራን በአለም ትልቋ ነዳጅ አምራች ስትሆን በየዓመቱ ወደ ውጭ የምትልከው የነዳጅ ዘይት በቢሊየን ዶላር ይገመታል።

የአገሪቱ የነዳጅ ዘይት ምርትና ዕድገት በአለም አቀፉ ማዕቀብ ጫና ስር ነው።

ማዕቀቡ በፍጥነት ተግባር ላይ እንደማይውል የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የወራት ማሳሰቢያ ቀነ-ገደብ አለው ብለዋል።

የኢራን ምላሽ ምን ይመስላል?

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጃቫድ ዛሪፍ አሜሪካ ወደ "ጠብ አጫሪነቷ" መመለሷን ገልፀው ነገር ግን ኢራን ለኒውክሌር ስምምነቱ መፍትሄ ለማፈላለግ ከሌሎች አጋር አገራት ጋር እየሰራች እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢራኑ ፕሬዚደንት ሃሰን ሮሃኒ በበኩላቸው ማይክ ፖምፔዮ የቀድሞ የሲኤአይ ኤ ኃላፊ ከመሆናቸው አንፃር በኢራንንና በተቀረው አለም ላይ ይህን መወሰናቸው ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ግላዊ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

የኒውክሌር ስምምነቱ ምን ነበር?

ኢራን ኒውክሌርን ለመስራት የሚያገለግለውን ዩራኒየምን መጠን ለመቀነስ ተስማምታ ነበር።

ይህም ለአስራ አምስት አመታት የሚሆን ለኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ና ለኒውክሌር መሳሪያ እንዲውል የታሰበ ነበር።

ፐሉቶኒየም የተሰኘ ለቦምብ መስሪያ የሚውል ኬሚካል አላመርትም በማለትም ተስማምታ ነበር።

በዚህም ሳቢያ በተባበሩት መንግስታት ፣ አሜሪካና ፣ የአውሮፓ ህብረት የተጣለባት ማዕቀብ የኢራን ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ አድርጎታል።

ስምምነቱ በኢራንንና በአምስት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ ፣ ቻይናና ሩሲያ እንዲሁም ጀርመን ጋር የተደረገ ነበር።