በጉጉት የሚጠበቀው የሁለቱ መሪዎች ጉባኤ ሊዘገይ ነው

ዶናልድ ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን Image copyright AFP

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የሚያደርጉት ጉባዔ ላይካሄድ ይችላል አሉ።

ጉባዔውን ለማካሄድ ሰሜን ኮሪያ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት፤ ካልሆነ ግን ጉባዔ ሊዘገይ እንደሚችል ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የደቡብ ኮሪያውን ፕሬዚደንት ሙን ጄ ኢንን በዋይት ሃውስ አግኝተው ባነጋጋሯቸው ጊዜ ነው።

ይሁን እንጂ ትራምፕ ሰሜን ኮሪያ ማሟላት ስላለባት ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀመጡት ዝርዝር ነገር ባይኖርም ከኒውክሌር ነፃ መሆኗ የግድ ነው ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያም በበኩሏ አሜሪካ ብቻዋን ኒውክሌር እንድናቆም የምትጫናቸው ከሆነ ጉባዔውን ልትሰርዝ እንደምትችል አስታውቃለች።

ከሳምንታት በኋላ በሲንጋፖር ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የሁለቱ መሪዎች ጉባዔ ታሪካዊ ነው።

ትራምፕ ምን ተናግረው ነበር?

ፕሬዚዳንቱ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በቀጣይ የሚያደርጉት ጉባዔ በተመለከተ "የሚሆነውን እናያለን" ብለው ነበር።

" እንዲሟሉ የምንፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ እነርሱ እንደሚሳኩ አስባለሁ ። የማይሆን ከሆነ ግን ጉባዔው አይካሄድም ። ስምምነት ውስጥ የገባነውም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆነን አይደለም" ሲሉም ገልፀዋል።

"ስምምነቱ ውስጥ የገባነውም ምርጫ ስላልነበረን ነው፤ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ይከሰታሉ፤ አንዳንዴም በቀላሉ ሊተገበሩ ይችላሉ" ሲሉም አክለዋል ።

ኪም ጆንግ ኡን ሃሳባቸውን የቀየሩትም ቻይናን ለሁለተኛ ጊዜ ከጎበኙ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ስለ ጉባዔው አዎንታዊ የሆነ አቋም እንዳላቸው ገልፀው "አሜሪካ ይህንን ታሪካዊ ጉባዔ እውን ለማድረግ ተግታ እየሰራች ነው፤ በሰሜን ኮሪያ ላይ ግፊት ለማድረግ ድጋፍ እያደረገችልን ነው" ሲሉ ቻይናን አመስግነዋል።