የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ስጋት ነግሶበታል

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ Image copyright Mizan-Tepi University

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሚዛን ካምፓስ ከእሁድ ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደ መሆኑንና ትምህርት መቋረጡን የዪኒቨርስቲው ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

ተማሪዎቹ የተቃውሞ ሰልፉን ማካሄድ የጀመሩት በሴት ተማሪዎች ላይ የመደፈር ሙከራ ከተፈፀመ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ከእሁድ አንስቶ ያለውን አለመረጋጋት ሸሽተው ከግቢው እንደወጡም ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ እንደሚሉት እሁድ እለት ሁለት ሴት ተማሪዎች መታጠቢያ ቤት ሳሉ ጩኸት መሰማቱንና ጭንብል ያጠለቀና ያላጠለቀ ወንዶች ሴቶቹን ለመድፈር መታጠቢያ ቤቱ ውስጥ ተገኝተው ነበር።

ጩኸቱን የሰሙ ተማሪዎች ተሯሩጠው ሲወጡ አንደኛው ወንድ የተማሪ ስልክ ይዞ ሮጠ።

የዩኒቨርስቲው ጥበቃ ጩኸቱን ሰምቶ በቦታው ተገኝቶ ስለነበር የሮጠውን ወንድ ይይዘዋል ብለው ቢጠብቁም እንዴት እንዳመለጠ አላወቁም።

"ልጁ ካመለጠ በኋላ ግቢው ድብልቅልቁ ወጣ። ድንጋይ ተወረወረ። ጥይትም ተተኮሰ" ስትል ስሜ አይገለጽ ያለች ተማሪ ገልጻለች።

ከግርግሩ በኋላ ገንዘብ ያላቸው ተማሪዎች ሆቴል ሲያድሩ ዘመድ ያላቸው ተማሪዎች ደግሞ ዘመዶቻቸው ጋር እንዳረፉ ከተማሪዋ ገለጻ መረዳት ችለናል።

የእሁዱ ተቃውሞ በሴት ተማሪዎች ቢጀመርም ወንድ ተማሪዎችም እንደተቀላቀሏቸውና የዩኒቨርስቲው ንብረትና ተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ተማሪዎቹ ገልጸውልናል።

ሌላ ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀች ተማሪ እንዳለችው የዩኒቨርስቲው ጥበቃዎች ወንድ ተማሪዎችን ለጥቃቱ ተጠያቂ ሲያደርጉ ሴት ተማሪዎች አጥቂዎቹ ከዩኒቨርስቲው ውጪ እንደመጡና ወንድ ተማሪዎች እጃቸው እንደሌለበት አሳውቀዋል።

ሴት ተማሪዎችን በመደገፍ የወጡ ወንዶች በጥበቃዎቹ ሲያዙ ሴት ተማሪዎች ተረባርበው እንዳስፈቷቸው የተናገረችው ተማሪ "አይናቸውን በድንጋይ የተመቱ አሉ። ሰባት ወንዶች በዘበኞች ተይዘው ሴቶች አስለቅቀዋቸዋል" ስትል ሁኔታውን አስረድታለች።

እሁድ የተጀመረው ተቃውሞ ሰኞ ሲቀጥል ከሴቶች መደፈር በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችን ለመግለጽ የተቃውሞ ሰልፉን የተቀላቀሉ ተማሪዎች እንደነበሩ ተማሪዎቹ አሳውቀዋል።

ሰⶉ እለት "መብታችን ይከበርልን፤ የጎደለ ነገር ይሟላልን፤" በሚል ባጠቃላይ የግቢው ተማሪዎች ተቃውሞ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ማክሰኞ ጠዋት የአካባቢው ማህበረሰብ "ተማሪዎቹ በመድፈር ወንጅለውን ስማችንን አጥፍተዋል" በሚል ዪኒቨርስቲው ውስጥ ገብተው ተማሪዎችን መደብደባቸውንም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

"ከዪኒቨርስቲው በላይ ያለ አማን የሚባል ከተማ ግርግር አለ። ዪኒቨርስቲው ውስጥ ምግብ ስለሌለ ጾማችንን ነው የዋልነው" የምትለው ተማሪ የአካባቢው ማህበረሰቦች እንዳይደበድቧቸው በመፍራት ከግቢው መውጣት ያልቻሉ ተማሪዎች እንዳሉም አክላለች።

በዩኒቨርስቲው የተነሳው ተቃውሞ ማክሰኞ ወደ አካባቢው መዛመቱን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

የቤንች ማጂ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወዳጆ ሱሌይማን በከተማዋ ግርግር መኖሩን ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን አረጋግጠዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም በግርግሩ ሳቢያ ሱቆች መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እንደሚሉት በቅጥር ግቢው ውስጥ ውሃ የለም፣ ግቢውም አጥር አልባ ነው። ሴት ተማሪዎች ልብሳቸውን ለማጠብ ወደ ወንዝ ሲሄዱም በተደጋጋሚ የመደፈር አደጋ እንደሚደርስባቸው አስረድተዋል።

አንዷ ተማሪ "ግቢው አጥር የለውም። የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ህንጻ ላይ ውሀ የለም፤ ግቢ ውስጥም ቧንቧ የለም፤ ስለዚህ በወራጅ ውሀ እንታጠባለን" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ወራጅ ውሀው ላይ የካፌ እጣቢ ስለሚገባበት ተማሪዎቹ ንጹህ ውሀ ለማግኘት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ከግቢው መውጣት እንዳለባቸው ገልጻለች።

ከግቢው በሚወጡበት አጋጣሚ የመደፈር አደጋ እንደሚደርስባቸውም ተማሪዋ አክላለች።

ተማሪዎቹ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስለችግሩ የታወቀው ተማሪዎች ከትንሳኤ በአል በኋላ ወደ ዩኒቨርስቲው ሲመለሱ ነው። የሴቶች መደፈር ዜና መናፈስ ከጀመረም ወራት ተቆጥረዋል።

ተማሪዎቹ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ስለመደፈር አደጋው ለዩኒቨርስቲው አመራሮች ቢያመለክቱም መፍትሔ አልተሰጣቸውም።

ተማሪዋ እንደተናገረችው ከዚህ ቀደም ሁለት ተማሪዎች ተደፍረዋል ከተባለ በኃላ የሴቶች ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ሆኖም ስለ ችግሩ የሚናገሩበት በቂ መድረክ አልተሰጣቸውም።

"እንድንናገር እድሉ አልተሰጠንም። ሊያዳምጡን አልቻሉም። ለዛሬ ይህንን ተናግራችኋል በቃችሁ። ሌላ ግዜ ደግሞ ትናገራላችሁ ተባልን። ስብሰባው ተካሂዶ መፍትሔውን ከወር በኃላ እናሳውቃችኋለን አሉን" ብላለች።

ሆኖም መፍትሔ ሳይሰጣቸው አሁን ላሉበት ሁኔታ መዳረጋቸውን ተማሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።