ካለሁበት 33፡ ኢትዮጵያዊው ''በተገንጣይቷ'' ካታሎንያ

Image copyright Yitagesu Zewedu
አጭር የምስል መግለጫ ይታገሱ ዘውዱ በስፔን ካታሎንያ

ይታገሱ ዘውዱ በሰሜን ምስራቅ ስፔን በምትገኘው ከሰሞነኛው የመገንጠል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ስሟ በሚነሳው ካታሎንያ ግዛት ውስጥ ነዋሪ ነው። ወደዚህ ስፍራ ያቀናው የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ሲሆን አመጣም በፖለቲካል ኢኮኖሚ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን በሮቬራ ቪርጂሊ ዩኒቨርሰቲ ለመከታተል ነው። ታሪኩን ከራሱ አንደበት እነሆ

ቁጥቦቹ የካቶሎያ ሰዎች

ስፔናዊያን እንደ ብዙዎቹ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ህዝቦች ሁሉ ከተቀረው የአውሮጳ ክፍል በተለየ መልኩ መዝናናት የበዛበት የኑሮ ብሂል ይከተላሉ።

የካታሎንያ ሰዎች ባህርይ ግን ትንሽ ይለያል። በባህላቸው ለቤተሰባዊ ኑሮ ከፍ ያለ ዕይታ ያላቸው የሀገሬው ሰዎች፣ ከተቀረው ማህበረሰብም ሆነ እንግዳ ጋር ለመቀራረብ ይቸግራቸዋል። ሆኖም ዘረኝነትን የመሳሰሉ ችግሮች አላየሁባቸውም።

የግዛቷ ነዋሪዎች ቀደም ብለው ያነሱት የመገንጠል ጥያቄ አሁን አሁን እየከሰመ ነው።የመገንጠል ጥያቄውን ሲያቀርቡ የነበሩ ወገኖችም ለእስር መዳረጋቸውን እንሰማለን። አሁን ያለው እንቅስቃሴ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን በማስፈታት ላይ ያነጣጠረ ነው።

ባለፈው ዓመት የጥቅምት ወር ውጥረቱ ጫፍ ነክቶ በነበረበት ወቅት በተለይ ካታሎኒያዊ ያልሆን ባዕዳን ስጋት ገብቶን ነበር።

Image copyright Yitagesu Zewedu
አጭር የምስል መግለጫ ከካታሎኒያ ማራኪ ዕይታ በትንሹ

"ምግብማ ሞልቷል ለኢትዮጵያዊ አይሆንም እንጂ!"

ብዙ ዓይነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁባቸው ምግቦች አሏቸው። ብዙዎች ምግቦች ግን በእኛ ሀበሾች ዐይን የምንጠየፋቸው ዓይነት ናቸው።

የአሳማ ስጋ፣ከባህር የወጡ እንስሳት እና ቀንድ አውጣን የመሰሉ ነፍሳትን ይበላሉ።

የወይራ ፍሬ በብዛት የሚመረትበት ሀገር ስለሆነ እሱን ማግኘታችን በተወሰነ መልኩ ያጽናናል።

ከሀገሬው ምግብ ጋር በበኩሌ ለመስማማት ቸግሮኛል፤ ስለሆነም ፓስታን የመሳሰሉትን አዘወትራለሁ። ከእንጀራ፣ሽሮ እና በርበሬ ርቆ መኖር ከባድ ነው።

Image copyright Yitagesu Zewedu
አጭር የምስል መግለጫ በሀገሬው ከሚዘወተሩ ምግቦች አንዱ

በህልማችን ሁሌም ሀገር ቤት ነው የምናድረው

ተወልጄ ያደግኩት ሻሸመኔ 81 የሚባል አካባቢ ነው።

ካደግኩበት ሰፈርም ሆነ ከመላ ሀገሬ ጋር በተገናኘ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል። ምግቡ፣መጠጡ፣የጓደኞቼ ወግ ይመጣብኛል።"ሁላችንም በህልማችን ሁሌም ሀገር ቤት ነው የምናድረው፣ ''ይባላል -የኔም ተመሳሳይ ነው።

ስለሀገሬ ሳስብ…እዚህ ሀገር ውስጥ ስኖር አንዳንድ የማያቸውን ነገሮች በሀገሬም በኖሩ ስል እመኛለሁ።

የመሰረተ -ልማት አውታራቸው የተሟላ ነው፤ በሦስት ዓመታት ቆይታየ መብራት ሲጠፋ የታዘብኩት አንድ ቀን ብቻ ነው።

የውሃ እጥረት የዘልማድ ችግሬ እንዳልነበር ሁሉ አሁን አሁን እየረሳሁ ነው።

የሀገራችን ፖለቲካ ከገባበት 'ቅርቃር' ወጥቶ ወደ ተሻለ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲያድግ፣ ዜጎች ሀሳባቸውን የሚገልጹበት በእኩልነት እና ፍትህ የሚኖሩባት ሀገር እንድትኖረን አበክረው ከሚሞግቱ እና ከሚመኙ መካከል አንዱ ነኝ።

ማህበራዊ ፍትህን በተመለከተም ዜጎች የሀገሪቱን ሀብት በእኩልነት ተጠቅመው፣በሀገራቸው ተከብረውና ታፍረው እንዲኖሩ እሟገታለሁ።

ዘረኝነት ፣የእርስ በርስ መጠፋፋት ተወግዶ እንደ ጥንቱ ተቻችለን የምንኖርበት ሀገር እንዲኖረንም እናፍቃለሁ።የናፈቅነው እንዲሳካም ይርዳን።

ተያያዥ ርዕሶች